“ስፖርት ኢኮኖሚን ለማሳደግ፣ የእርስ በእርስ ግንኙነትን ለማጠናከር እና ወዳጅነትን ለማጠናከር የላቀ ሚና አለው”አምባሳደር መስፍን ቸርነት::

0
205

ባሕርዳር: የካቲት 20/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የትምህርት ተቋማት በስፖርት የታነጸ ትውልድ ለማፍራት የሚያደርጉት ጥረት ውጤታማ እንዲኾን አስፈላጊው ድጋፍ ይደረጋል ሲሉ የባሕልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት ተናግረዋል። ሚኒስትር ዴኤታው ይህን ያሉት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የስፖርት ፌስቲቫል ማብሰሪያ መርሐግብር ላይ ነው።

የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፤ ስፖርት ኢኮኖሚን ለማሳደግ፣ የእርስ በእርስ ግንኙነትን ለማጠናከር እንዲሁም ከአገራት ጋር ወዳጅነትን ለማጠናከር የላቀ ሚና አለው።

የሀገርን ስም የሚያስጠሩ ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት ተከታታይነት ያለው ሥራ ማከናወን እንደሚገባ ጠቁመው፣ ለዚህም ትምህርት ቤቶች ትልቅ ድርሻ አላቸው ብለዋል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ያዘጋጀው የስፖርት ፌስቲቫል ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት የተያዘው ሀገራዊ ጥረት እውን እንዲኾን አጋዥ መኾኑን ገልጸዋል።

ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ጨምሮ ትምህርት ቤቶች በስፖርት የታነጸ ትውልድ ለማፍራት የሚያደርጉት ጥረት ስኬታማ እንዲኾን ሚኒስቴሩ ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት ረዳት ኮሚሽነር አትሌት ደራርቱ ቱሉ ሁላችንም ከትምህርት ቤት ተነስተን ለዚህ ደረጃ የበቃን በመኾኑ ትምህርት ቤቶች ለስፖርት ትኩረት ሊሰጡ ይገባል ብለዋል።

ከዚህ ቀደም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ይደረግ የነበረው ስፖርታዊ ውድድር መቋረጡን በማስታወስ ውድድሩ ቀጣይነት እንዲኖረው መሥራት እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ በበኩላቸው የስፖርት ፌስቲቫሉ በተጠናከረ ኹኔታ ቀጣይነት እንዲኖረው ለማስቻል የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎችን ማደስ፣ ደረጃ ማሻሻልና አዳዲስ ግንባታ ማከናወን ላይ በትኩረት እንደሚሠራ አብራርተዋል።

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በስሩ ባሉት ኮሌጆች የስፖርት ፌስቲቫል የሚያካሂድ ይኾናል።በስፖርት ፌስቲቫሉ ላይ በዩኒቨርሲቲው ስር የሚገኙ ኮሌጆች ይሳተፋሉ።ውድድሩ እግር ኳስ፣ ሩጫ፣ ቅርጫት ኳስን ጨምሮ የተለያዩ ስፖርቶችን ያካተተ ነው ተብሏል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here