“የባሕር ዳር ውበት እና ድምቀት”ብስክሌት እና የብስክሌት ስፖርት።

0
383

ባሕርዳር: የካቲት 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የብስክሌት ስፖርት እና ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የውድድር መድረክ ከ68 ዓመታት በላይ የዘለቀ ታሪካዊ ትስስር አላቸው፡፡ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1956 ለመጀመሪያ ጊዜ በተሳተፈችበት 16ኛው የሜልቦርን ኦሊምፒክ ጨዋታዎች በገረመው ደምቦባ (አፈሩ ይቅለለውና) ተወክላ በመሳተፍ ከአትሌቲክስ ስፖርት በመቀጠል በዓለም መድረክ በተደጋጋሚ ራሷን አስተዋውቃለች፤ ገጽታዋንም ገንብታበታለች።

ኢትዮጵያ በ2011 ዓ.ም በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የአፍሪካ ብስክሌት ሻምፒዮናን እንድታስተናግድ የአፍሪካ ብስክሌት ማኀበር ዕድል ሰጥቷት ውድድሩም በባሕር ዳር ከተማ መካሂዱ ይታወሳል። ውቢቷ ባሕር ዳር ከተማ መለያዋ ከኾኑት ነገሮች አንዱ ብስክሌት የሚዘወተርባት ከተማ መኾኗ ይጠቀሳል።

የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪዎች በቀደሙት ጊዜያት ብስክሌትን ጾታ እና ዕድሜ ሳይገድባቸው ብስክሌትን ይጋልቡ ነበር።እንደዛሬው ባጃጅና ታክሲ እንደልብ ባልነበረበት ጊዜ የከተማዋ ዋነኛ የመጓጓዣ አማራጭም ብስክሌት ነበር። ይሄ የነዋሪውና የብስክሌትን ቁርኝት የብስክሌት ውድድር በስፋት እንዲከናወንና ተወዳጅ እንዲኾንም ምክኒያት ኾኖ ቆይቷል።

አቶ ገብሩ የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ ናቸው። ከብስክሌት ጋር የፈጸሙትን “ጋብቻ” ረዥም ጊዜ እንደኾነው ይናገራሉ። ባሕር ዳር ከተማ ውስጥ የብስክሌት ትራንስፖርት እና የብስክሌት ስፖርት የአንድ ሳንቲም ኹለት ገጽታዎች ነበሩ ይላሉ።

እሳቸው ብስክሌት መጋለብ የጀመሩት የሰባተኛ ክፍል ተማሪ ሳሉ ነው። 12ኛ ክፍልን ጨርሰው በተከታታይ የትምህርት መርሐ ግብር በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ከመጀመሪያ እስከ ሁለተኛ ዲግሪ የተማሩት ወዲህ ብስክሌት እየተወዳደሩ ወዲያ የብስክሌት ትራንስፖርት እየተጠቀሙ እንደኾነ አስታውሰዋል።

“በአፍላ የወጣትነት ዘመኔ በባሕር ዳር ጨርቃ ጨርቅ ስፖርት ክለብ ታቅፌ ተወዳድሪያለሁ።ክለቡ ሲፈርስ ደግሞ በግል መወዳደር ቀጥየ ጥሩ ውጤት በማስመዝገብ ከከተማዋ ባለፈ በዞን ደረጃ ተወዳዳሪ ነበርኩ።ውድድር ሳይኖር እንኳ ለተሽከርካሪ እንዳናስቸግር ኾነን ሽርሽር እናደርግ ሲሉ ያስታውሳሉ።

ባሕር ዳር ከተማ ስትታሰብ የጣና ሐይቅ፣የአስፋልት ዳር ዘንባባዎች፣ ዓሳ እና በቅርብ ርቀት የሚገኘው የጭስ ዓባይ ፏፏቴ በማራኪ ገጽታቸው እንደሚታዎሱት ኹሉ ብስክሌትም ሌላው የከተማዋ መገለጫዋ (መታዎቂያዋ) ነበር ባይናቸው አቶ ገብሩ።

እንደ አቶ ገብሩ ቅዳሜ እና እሁድ በሁለቱም ጾታዎች በታዳጊዎች እና በአዋቂዎች እንዲሁም በግል እና በክለብ ደረጃ በየሳምንቱ ውድድሮች ይከናወኑ ነበር። ውድድሩ ደግሞ ከመዝናኛነቱ ባለፈ ሌሎች ፍላጎቱና ችሎታው ያላቸውን እያማለለ የሚያስገባ ፉክክር ና የተለየ ትርኢት ነበረውም ነው ያሉት። አሁን ግን ብስክሌት የሚያዘወትረው ሰው ቁጥር መቀነሱን አንደታዘቡ ይናገራሉ።

ነገር ግን ብስክሌት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንደንዳለው የሚገልጹት አቶገብሩ አቅሙ እና ችሎታው ያለው ኹሉ ብስክሌትን ቢጠቀም ወጭን በመቀነስ፣ ጤንነትን በመጠበቅ፣ ጊዜን በአግባቡ በመጠቀም እና የከተማዋን ገጽታ በበጎ እየገነባ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያገኝበታል ይላሉ ።

ሌላኛዋ የባሕር ዳር ነዋሪ ወይዘሮ ዓለምወርቅ ተዘራ ከሰኞ እስከ አርብ በየእለቱ ጠዋት እና ማታ 15 ኪሎ ሜትር ያህል በብስክሌት ተመላልሰው እንደተማሩ እና እዳስተማሩ አስታውሰዋል ።ተወዳዳሪም እንደነበሩ ጠቁመዋል። አንድ ልጅ ወልደውም ይወዳደሩ እንደነበር ያስታውሳሉ።

ከብስክሌተኛው ብዛት አንጻር ሕጻን ልጅ ሱቅ ሲላክ “ብስክሌት እንዳይገጭህ” ይባል እንደ ነበር አስታውሳለሁ፤አያይዘውም ከአንድ እስከ ሦሥት ጊዜያት ጸንሰው ሲወልዱ ምጥ እንዳልጠናባቸው ተናግረዋል። ምክንያቱ ደግሞ ብስክሌተኛ በመኾኔ ጡንቻዎቼ በቀላሉ ስለሚፍታቱ እንደኾነ ሐኪም ነግሮኛል ብለዋል።

የከተማዋ ውበትና ድምቀት የነበረው የብስክሌት ስፖርት በመቀዛቀዙ ማዘናቸውን ጠቁመው ለትንሳዔውም ወጣቱ ፊቱን ወደ ብስክሌት ማዞር ይገባዋል ብለዋል። ጉዳዩ የሚመለከታቸውን ባለደድርሻ አከላት ኹሉ መምከር ግድ ይላቸዋል ነው ያሉት።

በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የስፖርት ሳይንስ መምህር ዘመኑ ተሾመ (ዶ.ር) በባሕር ዳር ከተማ በቀደመው ዘመን የተሟሟቀ የብስክሌት ውድድር ይካሄድ ነበር፤ በየጊዜው ለዘርፉ የሚደረገው እገዛና ድጋፍ እየቀነሰ በመሄዱ ስፖርቱም ተቀዛቅዟል ብለዋል።

ዶክተር ዘመኑ አክለውም የብስክሌት ስፖርት እንዲያንሰራራ የብስክሌት ስፖርተኞችን የሚይዙ ክለቦች ያስፈልጋሉ። ክለቦች ሲኖሩ ውድድሮችም ይዘጋጃሉ። በጀትም ይመደብላቸዋል፤ ክለቦቹ ተወዳዳሪ እና አሸናፊ ሊያደርጓቸው

የሚችሉ ዘመናዊ ብስክሌቶችንም ይገዛሉ፤ አሠልጣኞችንም ይቀጥራሉና ብለዋል።በዚህ መልኩ ተተኪዎች እየፈሩ ስፖርቱም እየተለወጠ እና እያደገ ይሄዳል። እናም ተቀዛቅዞ እየተዳከመ የሚገኘውን የብስክሌት ስፖርት ወደ ከፍታው መመለስ የሚቻለው ሁሉም በቀናነት የሚጠበቅበትን በርብርብ ሲያከናውን ነው በማለት ሙያዊ ምክራቸውን ለግሰዋል።

የባሕር ዳር ከተማ ተቀዳሚ ከንቲባ አቶ ጎሹ እንዳላማው ለአሚኮ በሰጡት ሀሳብ ብስክሌት እንዲስፋፋ የመሠረተ ልማት ግንባታዎችን ምቹ ማድረግ ይገባል።ለዚህም ነው እየተገነቡ ያሉትን መንገዶች ለብስክሌት ታሳቢ እየተደረጉ ያሉት ብለዋል።አቶ ጎሹ አክለውም ተገንብተው የተጠናቀቁት መንገዶችም ቢኾኑ ሰፊ በመኾናቸው የብስክሌት መስመር አንዲኖራቸው እየተሠራ ይገኛል ነው ያሉት።

በባሕር ዳር ከተማ በተሠረጡ ቦታዎች ላይ ብስክሌቶች እንዲቆሙ በማድረግ መጋለብ የሚፈልግ ቱሪስት ኹሉ ሊከራይ የሚችልበት አሠራር ይዘረጋል።በዚህ መልኩም የብስክሌት ተጠቃሚውን ቁጥር ለማብዛት መታሰቡን ከንቲባው ገልጸዋል።

ከተማ አሥተዳድሩ የብስክሌትን ተጠቃሚውን ቁጥር ለማብዛት “ሽርሽር በሳይክል” በሚል የተጀመረ ሥራ መጀመሩንም ተናግረዋል። የብስክሌት ስፖርትን ለማስፋፋት የመንግሥት ሠራተኞች፣ አመራሮች፣ ነጋዴዎች አንዲሁም ልዩ ልዩ የማኀበረሰብ አባላት በቅንጅት ፕሮጀክቱን ማበረታታት እና መደገፍ ይገባቸዋል ብለዋል። እንዲህ ከተሠራ የተቀዛቀዘው የባሕር ዳር መለያ የብስክሌት ስፖርት ይነቃቃል፤ ይሟሟቃል፤ ወደ ከፍታውም ይመለሳል ነው ያሉት።

ዘጋቢ:መሉጌታ ሙጨ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here