ባሕርዳር: የካቲት 07/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የ31ዓመቱ ሄሪቲየር ሉቩምቡ የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ብሔራዊ ቡድን የመስመር ተጫዋች ነው፡፡
ተጫዋቹ እግር ኳስ መጫወት ከጀመረበት እንደ አውሮፓውያኑ ዘመን 2014 ጀምሮ በሀገር ውስጥ ውድድር በሚያሳየው ድንቅ የሜዳ ላይ ብቃት ብዙዎቹን አስደምሟል፡፡
በማራኪ ችሎታው በተሳቡ የተለያዩ ሀገራት ቡድኖችም እየተመረጠ ተጫውቷል፤ እየተጫወተም ይገኛል፡፡ ለአብነት ከ2022 ጀምሮ በሩዋንዳ ፕሪሜየር ሊግ ለራዮን ቡድን እየተሰለፈ ይገኝ ነበር፡፡
ከሰሞኑ ታዲያ በሩዋንዳ ፕሪሜየር ሊግ የራዮን ስፖርትስ ከፖሊስ ኤፍ ሲ ጋር ይጫወታሉ፡፡ በዚህ ወቅት ሉቩምቡ በቅጣት ምት አስደናቂ ግብ ካስቆጠረ በኋላ በጣቱ ምልክት አሳየ፡፡ የምልክቱ ትርጉም ደግሞ እግርኳስ ከሚጠይቀው ሥነምግባር ውጭ የኾነ ነበር፡፡
የሩዋንዳ እግር ኳስ ማኅበርም ጉዳዩን በዝምታ አላለፈውም፤ የምልክቱን ትርጉምና ተምሳሌት መርምሮ ተጫዋቹን “የስፖርታዊ ሥነ ምግባርን ጥሰሃል“ በሚል ከጨዋታ አግዶታል፡፡
አከታትሎም ባወጣው መግለጫ “እኛ አንድም ስፖርተኛ በእግር ኳስ ውስጥ የትኛውንም ይዘት ያላቸውን ምልክቶች ወይም ቃላት እንዳይጠቀም በሕግ ከልክለናል፤ በተለይ የውጭ ሀገር ተጫዋች እኛ ሀገር ውሰጥ ኾኖ የየትኛውንም ሀገር ሕዝብ ክብር እንዲነካ አንፈቅድም” ብሏል።
ራዮን ስፖርትስ ክለብም “በጥባጭ ተጫዋች አያስፈልገንም“ በሚል የሄሪቲየር ሉቩምቡ የስምምነት ውል እንዲቋረጥ አድርጓል፡፡
በሙሉጌታ ሙጨ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!