ባሕር ዳር: የካቲት 06/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የኮትዲቯሩ የአፍሪካ ዋንጫ ከመጀመሩ በፊት ግርማቸው የሚያስፈራውን ሞሮኮ፣ ሴኔጋል እና ግብጽ የመሳሰሉ ቡሔራዊ ቡድኖችን ዛሬ ላይ ከሚዛናቸው አውርዷል።
ከተሳትፎ የዘለለ አቅም የላቸውም የተባሉት አንደ ደቡብ አፍሪካ ዓይነት ብሔራዊ ቡድኖች ደግሞ ከኮትዲቯር ጥሩ ትዝታን አትርፈዋል። ከምንም በላይ ከምድቧ በቀጥታ ማለፍ አቅቷት ወድቃና ተነስታ የዋንጫ ባለቤት የኾነችው ኮትዲቯር “ለእኔ ያለውን ወፍ አይቅምሰውም” አባባልን አውነትነት አረጋግጣ ብዙዎችን አስደምማለች።
እንደ ብሔራዊ ቡድኖች ሁሉ በግለሰብ ደረጃ ተጫዋቾች በውድድሩ ደምቀው እና ደክመው ታይተዋል። መሐመድ ሳላህ፣ ሳድዮ ማኔ፣ ቪክቶር ኦስሚን እና የመሳሰሉ ኮከቦች በተሳተፋበት ውድድር ብዙ የማይታወቁት ዊልያም ትሮስት ኢኮንግ፣ ሮንዊን ዊሊያምስ እና ሲሞን አዲንግራ ጎልተው መውጣታቸው ለዚህ ማሳያ ነው።
ስለነዚህ ኮከቦች በስፋት በሚወራበት በዚህ ወቅት ነገርን ነገር ያነሳዋል እንዲሉ ከወዲህ የአንድ ወቅት የአፍሪካ ዋንጫ ኮከቡን ታሪክ በጨረፍታ እንመልከት። ሰውየው በኢትዮጵያ እግር ኳስ ዘመን የማይሽረው ታሪክ ባለቤት ነው። በቅዱስ ጊዮርጊስ ከብሯል፣ በአፍሪካ ዋንጫ ደምቋል – ዝነኛው መንግሥቱ ወርቁ። ሦስተኛው የአፍሪካ ዋንጫ ሲነሳ ቀድመው ከሚመሰገኑት የወቅቱ የአፍሪካ ኮከቦች ቀዳሚው ነው፤ የውድድሩ ኮከብ ግብ አስቆጣሪ እና ኮከብ ተጫዋች የቀደሙ አሻግራቸው የኋላው መንግሥቱ ወርቁ።
በትምህርት ቤት ስፖርት የተጀመረው የመንግሥቱ የእግር ኳስ ሕይዎት በአፍሪካ ዋንጫ ከታዩ ምርጥ አጥቂዎች አንዱ እስከመኾን አድጓል። ቆየት ያሉትን ልሳነ ጊዮርጊስ ጋዜጣ፤ ገነነ መኩሪያ ከመንግስቱ ጋር ያደረገው ምልልስ በሰነድ የተዘጋጀ እና አዲስ ዘመን ጋዜጣን በዋቢነት የሚጠቅሱ የተለያዩ ምንጮች የመንግስቱን እግር ኳስ አዋቂነት በስፋት አትተዋል።
በትምህርት ቤት እና በሰፈር ቡድን ባሳዩት ድንቅ ብቃት ጊዮርጊስን ተቀላቅሎ በፈረሰኞቹ ቤት ለ16 ዓመታት ተጫውቷል። በችሎታው ከክለቡ ጋር በርካታ ድሎችን አሳክተዋል። በክለቡ ደጋፊዎች ስማቸው አሁንም ድረስ ይዘመራል፤ በእግር ኳስ አፍቃሪያን ዘንድም ስሙ ከመቃብር በላይ ይነሳል። ያለ ደሞዝ ያገለገለው የጊዮርጊስ ክለብም መንግሥቱ ይለብሰው የነበረውን 8 ቁጥር መለያ ለእሱ መታሰቢያ አድርጎ ይዘክረዋል።
ሜዳ ውስጥ እልኽኛ እና ሽንፈትን የማይወድድ እንደነበር የሚነገርለት መንግሥቱ በተለያዩ የአውሮፓ ክለቦች ተፈላጊም ነበር። በፈረንሳይ ክለቦች ዓይን ከመግባትም በላይ በጣሊያኑ ኃያል ክለብ ኤሲሚላን በጥብቅ ተፈልጎ ነበር። ነገር ግን ጣሊያን ጀግናውን “ባሪያ” ልታደርግ ነው ተብሎ በንጉሡ ሳይቀር ቁጣን በመፍጠሩ ሃሳቡ ሳይሳካ ቀረ።
በወቅቱ እግር ኳስ የዳቦ መቁረሻ ሳንቲም አያስገኝም። በዚህ ምክንያት መንግሥቱ ከእግር ኳስ ጎን ለጎን መብራት ኃይል ውስጥ ተቀጣሪ ሠራተኛ ነበረ። ነገር ግን በ1955 ዓ.ም ቅዱስ ጊዮርጊስ ከመብራት ኃይል ቡድን ጋር ሲጫወት ጊዮርጊስ 4 ለ 1 አሸነፈ። በጨዋታው የመብራት ኃይሉ ሠራተኛ መንግስቱ መብራት ኃይል ላይ ሦስት ግብ አስቆጠሩ።
ከጨዋታው በኋላ የመብራት ኃይል ሠራተኞች ደሞዝ በምንከፍለው ሠራተኛችን እንዴት እንዋረዳለን ብለው ይቆጫሉ። የተቋሙ ኋላፊዎችም መንግስቱ ለመብራት ኃይል እንዲጫወት ጠየቁት። መንጌ ግን ከጊዮርጊስ ውጭ አይኾንም ብሎ ከሥራ ተሰናብቷል።
“መንግሥቱ ወርቁ የኳሱ ንጉሥ
የጎንደር ሰው ነው ያውም የቋራ
ሃሞተ ኮሩ ልበ ተራራ” የተባለለት መንግሥቱ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እስካሁን ያልተደፈረ ታሪክ ባለቤት ነው። ለመጀመሪያ ጊዜ አረንጓዴ ቢጫ እና ቀይ መለያውን የለበሰው በ1951 ዓ.ም ነው። እስከ 1964 ዓ.ም በነበረው የብሔራዊ ቡድን ቆይታም 102 ጊዜ ተጫውቷል። 62 ግቦችን ሲያስቆጥር እስካሁን ድረስ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ እሱ ነው።
በተለይ በሦስተኛው የአፍሪካ ዋንጫ የነበረው ትልቅ ድርሻ ብቸኛ የኾነው የሀገራችን የመድረኩ ድል ሲታወስ ስሙ ከፍ ብሎ እንዲነሳ አድርጎታል። በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት በተካሄደው የያኔው የአፋሪካ ዋንጫ የፍጻሜው ጨዋታ ከግብጽ ጋር የተደረገ ነበር።
የግብጽ ብሔራዊ ቡድን 1ኛ እና 2ኛውን ዋንጫ በማሸነፍ ለመረታት የማይታሰብ ቡድን መኾኑን አሳይቷል። የመጀመሪያውን ዋንጫ ሲያነሳ ደግሞ ኢትዮጵያን በሰፊ ግብ አሸንፎ ነበር።
ተመልካቹ ግብጽን ለመበቀል ጥሩ አጋጣሚ አድርጎታል፤ የማይደፈር የመሰለው የግብጽ ኃያልነት ሲታሰብ ደግሞ ሌላ ስጋት። ጨዋታውን ንጉሡን ጨምሮ በርካታ ተመልካች ታድሞበታል። በኢትዮጵያ በኩል “ማሸነፍ ብቻ” በሚል በተገለጸው ጨዋታ “በግብጽ መሸነፍ ያመናል” በሰፊው ስታዲየሞ ተሰምቷል።
በጨዋታው ግብጾች ግብ የማስቆጠር ቅድሚያ ቢወስዱም የማታ ማታ ድሉ ለሐበሾች ኾኗል። ይህ ድል እንዲገኝ መንግሥቱ በፍጻሜው ግብ ከማስቆጠር በተጨማሪ በውድድሩ ምርጥ ብቃት አሳይቷል።
በሦስት ግቦች የውድድሩ ከፋተኛ ጎል አስቆጣሪ እና የውድድሩ ምርጥ ተጫዋች መንግሥቱ ነበር። ኢትዮጵያዊ ኾነው በአፋሪካ ዋንጫ እነዚህን ክብሮች ያሳካ ብቸኛው ሰው እስካሁን ድረስ መንግሥቱ ነው። በአፍሪካ ዋንጫ ታሪክ ብዙ ግብ ካስቆጠሩ ተጫዋቾች መካከልም መንግሥቱ ወርቁ ስሙ በታሪክ ሰፍሯል። 10 ግቦችን በማስቆጠር 4ተኛው የውድድር መድረኩ የምንጊዜም ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ነው መንግሥቱ።
ምርጥ ተጫዋች ምርጥ አሠልጣኝ ላይኾን ይችላል። መንጌ በአሠልጣኝነት ሥራውም የሚቀናበት ታሪክ ባለቤት ነው። ቅዱስ ጊዮርጊስ እና መብራት ኃይልን በመሳሰሉ ክለቦች በአሠልጣኝነት አንቱ የሚያሰኝ ሥራ ሠርቷል። የኢትዮጵያን ብሔራዊ ቡድንም በአፋሪካ ዋንጫ መድረክ ሳይቀር መምራት የቻለ ድንቅ አሠልጣኝ ነበር።
በተጨማሪም በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ኢንስትራክተር በመኾን ሠርቷል። ከሀገር አልፎ ናይጀሪያ፣ ኡጋንዳ እና ሲውዘርላድን በመሳሰሉ ሀገራት ተዘዋውሮ አሠልጣኞችን አሠልጥኗል። ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ አሠልጣኞችን አፍርቷል።
አባቱም ፊታውራሪ ወርቁ ስንቄ በአምስት ዓመቱ የጣሊያን ወረራ ወቅት ፋሽስትን መቆሚያ መቀመጫ ያሳጡ ድንቅ አርበኛ ነበሩ። ፋሽስት ፊታውራሪ ወርቁን ለመያዝ በሚል መንግሥቱን እና እናቱን በእስር አንገላትቷል። ጀግና አባቱ ያወጡለት ስም “አሻግራቸው” ወደ መንግሥቱ የተቀየረውም ከእናቱ ጋር በእስር በነበሩበት ወቅት ነው። ምክንያቱ ለምን እንደኾነ ባይታወቅም።
በእነ መንግሥቱ ጊዜ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫ ባለቤት ኾናለች። መንግሥቱም የአፍሪካ ዋንጫ ምርጥ ተጫዋች እና ኮከብ ግብ አግቢ ነበር። በአፋሪካ ዋንጫ ታሪክ አሁንም ድረስ በ10 ግቦች አራተኛው ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ነው።
አሁን ኢትዮጵያ በመሠረተችው ውድድር ለመሳተፍ ተቸግራለች። እንደ መንግሥቱ ስሟን የሚያስጠራ ኮከብ የአብራክ ክፋይም ገና እየፈለገች ነው። መሠራት ካለበት የቤት ሥራ በተጨማሪ ትናንት የዛሬ ስንቅ ነውና የትላንቶቻችን ጀግንነት ማወቅ እና መማር ቢጠቅም እንጅ አይጎዳም። እግር ኳስ አብዝቶ በሚወደድበት የሐበሻ ምድር የኮከቡ መንግሥቱ ወርቁ ሥም ሁሌም ይታወሳል።
በአስማማው አማረ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!