የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች ዛሬ ይጀምራሉ።

0
578

ባሕርዳር: የካቲት 05/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የየምድብ አሸናፊዎችን ከለየ በኃላ ከውድድር ርቆ ሰንብቷል።ከዛሬ ጀምሮ ደግሞ ለሩብ ፍጻሜ የሚበቁ ቡድኖችን ለመለየት የሚደረጉ ጨዋታዎች ይካሄዳሉ።

በምሽቱ መርሐ ግብር የአምናው የዋንጫ ባለቤት ማንቸስተር ሲቲ ወደ ዴንማርክ ተጉዞ ኮፐንሀገን ጋር ሲጫወቱ፣የምንጊዜም የውድድሩ ባለታሪክ ሪያል ማድሪድ የጀርመኑን አርፒ ሊፕዚንግን ከሜዳው ውጭ ይገጥማል።

ማንቸስተር ሲቲ በምድብ ጨዋታዎች የምድቡን ሁሉንም ጨዋታዎች ማሸነፍ ችሏል።በምሽቱ ጨዋታ ከጉዳት የተመለሰው ሀላንድን ጨምሮ ሁሉም ወሳኝ ተጫዋቾች ለጋርዲዮላ ምርጫ ዝግጁ መኾናቸውን ቢቢሲ በስፓርት ገጹ አስነብቧል።

የዴንማርኩ ኮፐንሀገን በጠንካራው ምድብ አንድ ባየርሙኒክን በመከተል ጥሎ ማለፍን መቀላቀሉ ይታወሳል።ማንቸስተር ዩናይትድንና ጋላታሳራይን በልጦ እዚህ መድረሱ ቡድኑ ቀላል ተጋጣሚ ላለመኾኑ ማሳያ ነው።

በሌላኛው የምሽት ጨዋታ አርቢ ሊፕዚንግ ሪያል ማድሪድን ያስተናግዳል።ማድሪዶች ሁሉንም የምድብ ጨዋታዎች መርታታቸው ይታወሳል።በላሊጋውም ወጥ የኾነ ጉዞ ላይ ናቸው።በርካታ ተጫዎቾቻቸው ጉዳት ላይ መገኘታቸው ለነጮቹ የዛሬ ስጋት ነው።

ሊፕዚንግ በምድብ ሰባት ሲቲን ተከትሎ ነው ጥሎ ማለፉን የተቀላቀለው።በዛሬው ጨዋታ የማድሪዶች በጉዳት መሳሳት ድል ለማድረግ ያነሳሳቸዋል ተብሏል።ሻምፒዮንስ ሊጉ ነገ በሁለት ጨዋታዎች ሲቀጥል ቀሪ ጨወታዎች ከሳምንት በኃላ ይቀጥላሉ።

በአስማማው አማረ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here