ለክልሉ የስፖርት ቡድኖች መፍረስ ተጠያቂው ማን ነው?

0
270

ባሕር ዳር: የካቲት 01/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በበርካታ የሕዝብ እና የመንግሥት ሃብት ተቋቁመው ለዓመታት ለኀብረተሰቡ ዘርፈ ብዙ ጥቅም ሲያስገኙ የነበሩ ቡድኖች እንደዘበት ሲፈርሱ በመመልከታቸው እንዳዘኑ ተመልካቾች፣ ስፖርተኞች እና ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡

ዮናታል ፍቅሩ የደሴ ከተማ ነዋሪ ናቸው። እሳቸው እንዳሉት በደሴ፣ በኮምቦልቻ፣ በደብረ ብርሃን እና በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ የተለያዩ ቡድኖች እየተዘዋወሩ እግር ኳስ ተጫውተዋል። ይሁን እና በአማራ ክልል በተለያዩ ከተሞች እሳቸው ያኔ የተጫወቱባቸው የኮምቦልቻ ጨርቃ ጨርቅ፣ ጥቁር ዓባይ፣ ደብረ ብርሃን ብርድ ልብስ ፋብሪካ እና ሌሎችም ስመ-ገናና ቡድኖች ፈርሰዋል። የቡድኖቹ መፍረስ ደግሞ ታዳጊዎች ትኩረታቸውን ስፖርት ላይ እንዳያደርጉ አድርጓቸዋል፡፡

“እኔ እግር ኳስ የማሠለጥናቸው 31 ወንድ እና 18 ሴት ሠልጣኝ ልጆች አሉኝ፤ ነገር ግን ደሴ ከተማ ውስጥ በየጊዜው ክለቦች በመበተናቸው ወላጆች ልጆቻቸውን ወደ ሥልጠና ሜዳ ለመላክ ፈቃደኛነታቸው ቀንሷል፡፡ 11 ወንድ እና 8 ሴቶች ልጆች ሥልጠናውን ጀምረው አቋርጠዋል። የእነዚህ ልጆች ውሎም አልባሌ ስፍራ በመሄድ የጫት ሱስን ሲለማመዱ አስተውያለኹ፤ አንዷማ ልጅ ሥልጠናዋን አቋርጣ በሰዋራ ስፍራ ጫት መሸጥ መጀመሯን ከሰዎች ሰምቼ [ስመለከት] የሌሎችንም ውሎ በእሷ ውስጥ እያሰብሁ በጣም አዝኛለሁ…ለዚህ ሁሉ ዳፋው የክለቦች መፍረስ አድርጌም ወስጀዋለሁ” ብለዋል፡፡ ስለዚህ ቡድኖች ሲፈርሱ ሁሉም በይመለከተናል ስሜት ለምን ብሎ መሥራት ይጠበቅብናል ብለዋል አቶ ዮናታን።

አቶ ዋለልኝ ካሣ የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ ናቸው። እኝህ ሰው ስፖርት ሳይንስ ተምረው በአንድ የመንግሥት መሥሪያ ቤት ውስጥ ስፖርት ላይ ይሠራሉ።

የቀድሞው የአማራ ውኃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት የአሁኑ የውኃ ሥራዎች ኮርፖሬሽን የእግር ኳስ ቡድን ደጋፊና የደጋፊዎች ማኅበር አባል በመኾን ለቡድናቸው የሚኾን መዋጮ ያዋጡ እንደነበር አስታውሰዋል አቶ ዋለልኝ፡፡ ቡድኑ በአንደኛ እና በከፍተኛ ሊግ ተሳታፊ በነበረባቸው ወቅቶች ከሜዳው ውጭ የሚያደርጋቸውን ጨዋታዎች ሳይቀር በመሄድ ይደግፉ ነበር፡፡ በዚህም የአውሥኮድ ጨዋታ ከመዝናኛነቱ ባሻገር ለአገልግሎት ሰጭ ተቋማትም የገቢ ምንጭ ኾኖ ነበር ይላሉ።

የክለቡ መኖር በዘርፉ ታላላቅ ስፖርተኞች እንዲፈልቁም አድርጓል ባይ ናቸው:: ለአብነትም፦ የአሁኑ የባሕር ዳር ከተማ እግር ኳስ ክለብ አሠልጣኝ ደግአረገ ይግዛው፣ የቀድሞው ተጫዋቹ የአሁኑ የአውስኮድ አሠልጣኝ እንዳወቀ አጥናፉ እና የባሕር ዳር ከተማው ተከላካይ ያሬድ ባዬም ከዚህ ቡድን የወጡ ስፖርተኞ እንደኾኑ ጠቁመዋል አቶ ዋለልኝ።

ቡድኑ ከእግር ኳስ በተጨማሪ በተለያዬ የዕድሜ ደረጃ ለታዳጊዎች ሥልጠና ይሰጣል ያሉት አቶ ዋለልኝ፤ እነዚህ ወጣቶች ነገን በብሩህነቱ አሻግረው ይመለከቱ እንደነበር የ15 ዓመት ልጃቸውን በምሳሌነት ጠቅሰዋል። አሁን ግን ቡድኑ በመፍረሱ ልጃቸው ሥልጠና አቋርጦ ፊቱን ከጓደኞቹ ጋር ወደ “ቨርቹዎል ጌም” አዙሮ የማይበጀውን ነገር መለማመዱን በክትትል አረጋግጫለሁ፤ ደግነቱ በተግሳጽ መልሸዋለሁ እንጂ ብለዋል። “የክለቦች መፍረስ እያስከተለው ያለው ችግር ዘርፈ ብዙ መኾኑንም ከልጄ ተረድቻለሁ ” ሲሉ አቶ ዋለልኝ ተናግረዋል፡፡

የቀድሞው የአማራ ውኃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት የአሁኑ የውኃ ሥራዎች ኮርፖሬሽን የእግር ኳስ ቡድን የበጀት እጥረት በዋናነት ለክለቡ እድገት መሰናክል እንደኾነ የስፖርት ክለቡ ሥራ አስፈፃሚ ሠብሣቢ ጥላሁን አማረ ገልጸዋል፡፡ ለስፖርተኞች ደመወዝ መክፈል፣ አዳዲስ ስፖርተኞችንም ወደ ስፖርት ክለቡ ለማምጣት አቅም እንዳነሳቸው አብራርተዋል::

የሥራ አስፈጻሚ ሠብሣቢው ጥላሁን ጨምረው እንዳሉት የ2015 ዓ.ም የክለቡ እንቅስቃሴ በተገመገመበት ወቅት ክለቡ ለአዲሱ የውድድር ዘመን [2016 ዓ.ም] ዝግጅት እንዲጀምር በቃለ ጉባኤ ተይዞና ተወስኖ እንደነበረ አስታውሰዋል። ይሁንና በቃለ ጉባኤ የተወሰነው ሐሳብ ተቀይሮ በበጀት እጥረት ምክንያት የስፖርት ቡድኑ ሥራ እንዳይጀምር በይደር መያዙን ገልጸዋል፡፡ የስፖርት ቡድኑ በየዓመቱ 12 ሚሊዮን ብር ይመደብለት እንደነበርም በማስታወስ፡፡

አቶ ይከበር መንግሥት በደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር የስፖርት ባለሙያ ናቸው። “በከተማ አሥተዳደሩ ስር ተመዝግበው በልዩ ልዩ ውድድሮች እየተሳተፉ የነበሩትን ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ እና የመንቆረር ኮንስትራክሽን ቡድኖች ለመፍረስ ሲቃረቡ ‘ለምን ? ብለን ጠይቀናል፤ ለመደገፍም ሞክረናል፤ ነገር ግን ቡድኖቹ የገጠማቸው የበጀት እጥረት በእኛ አቅም የምንፈታው ኹኖ አላገኘነውም፤ ጉዳዩንም በተዋረድ እስከ ክልል ድረስ በማሳወቃችን ግዴታና ኀላፊነታችንን ተወጥተናል ስለዚህ የችግሩ መፍቻ ቁልፍ ያለው ክልሉ ላይ ነው” ይላሉ።

በአማራ ክልል ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ የስፖርት ማኅበራት ዕውቅናና ድጋፍ ዳይሬክተር ሙሉጌታ ሉሌ በበኩላቸው “በአማራ ክልል የተለያዩ ቡድኖች እየፈረሱ ነው፡፡ እነዚህ ቡድኖች ሲፈርሱ በዞን ደረጃ ያሉ መሪዎች “ለምንድን ነው የሚፈርሱት ?” በማለት ጠጋ ብለው ማገዝና መሞገት አለባቸው ብለዋል፤ ቡድኖች የኀብረተሰቡ ሃብት ናቸውና።

በክልሉ የሚገኙ የልማት አጋር ድርጅቶች መነሻቸው ሕዝብ ተኮር ስለኾኑ ለሕዝብ ማበርከት ከሚገባቸው በርካታ ነገሮች በጣም ጥቂቱ ነገር ነው የስፖርት ቡድን መያዛቸው። ያቋቋሙትን ቡድን ደግሞ ደግፎ መዝለቅ የውዴታ ግዴታቸው ነው።

አሁን ላይ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ አንድ ተጫዋች ለፊርማ ሰባት ሚሊዮን ብር እየተከፈለው ነው።ታዲያ ክለቦቻችን ባይፈርሱና በክልሉ የሚገኙ ወጣቶችን በተለያዩ የስፖርት ዓይነቶች ኮትኩተው ቢያሳድጉ ለፊርማ ከሚወጣው ሰባት ሚሊዮን ብር ልጆቻችንን ተከፋይ ማድረግ ይቻላል። እናም ቡድኖች እንዳይፈርሱ ወረዳዎች እና ዞኖች ከፍተኛ ኀላፊነት አለባቸው። በእኛ[በክልል] በኩል ቡድኖች እንዳይፈርሱ በትጋት እየሠራን ነው ብለዋል።

በክልሉ ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ የስፖርት ዘርፍ ምክትል ቢሮ ኀላፊ ጋሻው ተቀባ እንዳሉት ከዞን፣ ከወረዳ፣ ከከተማ አሥተዳደር ኀላፊዎች እና ከንቲባዎች እንዲሁም ከቦርድ ሠብሣቢዎች ጋር በይዞታቸው ስር ያሉ ቡድኖች እንዳይፈርሱ ይልቁንም ተጠናክረው አመርቂ ውጤት በሚያስመዘግቡበት ስልት ዙሪያ እየተወያየን ነው፤ በውይይቱ ከአንዳንዶቹ ጋር ቶሎ ተግባብተናል ብለዋል፡፡

ለአብነትም የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ሊፈርስ የነበረውን የቅርጫት ኳስ ቡድን ወደ ውድድር መልሶታል ሲሉ ተናግረዋል፡፡ እንደ አውስኮድ ያሉትም በ2017 ዓ.ም የውድድር ዘመን ተሳታፊ እንዲኾኑ የምዝገባ ሥራ ከወዲሁ እያከናወን ነው ብለዋል አቶ ጋሻው፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here