“በልኩ የማይገኘው የእንግሊዝ ታላቁ የእግር ኳስ ደርቢ” ሊቨርፑል ከማንቼስተር ዩናይትድ

0
396

ባሕር ዳር: ታኅሳስ 6/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ሊቨርፑል እና ማንቼስተር ዩናይትድ በእንግሊዝ እግር ኳስ የከበረ ዝና ባለቤቶች ናቸው። በአውሮፓ ውድድሮችም እንግሊዝ ከሁለቱ ቀያዮች የተሻለ ውጤታማ ክለብ የላትም።

ይሄ ውጤታማነታቸው በክለቦቹ መካከል ዘመን የተሻገረ ተቀናቀኝነትን ፈጥሯል። አንዱ ከሌላው ተሽሎ ቀዳሚው የአንግሊዝ ክለብ ለመኾን ባደረጉት ሩጫ እርስ በርሳቸው የከረረ ፉክክር ውስጥ ገብተዋል።

ለጊዜው ዩናይትድ ፕሪሜር ሊጉን 20 ጊዜ በማንሳት ግርማው ከፍ ያለ ነው። በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ደግሞ ሊቨርፑል አምስት ጊዜ በመንገስ ውጤታማው የእንግሊዝ ተወካይ ኾኗል።

አንደ ቢቢሲ ስፓርት መረጃ ሁለቱ ክለቦች በመላው ዓለም የብዙ ደጋፊ ባለቤት ናቸው። በዚህም ምክንያት የሁለቱ ክለቦች የእርስ በእርስ ጨዋታ ከእንግሊዝ አልፎ በመላው ዓለም በጉጉት ይጠበቃል። ጨዋታውን ለማሸነፍ የሚደረገው የሜዳ ውስጥ ትንቅንቅ እና የደጋፊዎች የድጋፍ ትርዒትም ለሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ድምቀት ኾኖ ይነሳል።

የሁለቱ ክለቦች ተቀናቃኝነት ዩናይትድ ውጤታማውን አሠልጣኝ ሰር አሌክስ ፈርጉሰንን ካገኘ በኃላ ይበልጥ ማየሉ ይነገራል። ፈርጉሰን ኦልትራፎርድ ሲደርሱ ሊቨርፑል የእንግሊዝ ኃያሉ ክለብ ነበር። ቆፍጣናው አሰልጣኝ “ማንቼስተር የተገኘሁት የሊቨርፑልን የበላይነት ለመግታት ነው” ብለው በጋዜጦች ሳይቀር መሳለቂያ ኾነው ነበር።

ዩናይትድ በሰውየው አመራር ጠንክሮ ዋንጫ ማንሳት መጀመሩን ተከትሎም የሁለቱ ክለቦች ተቀናቃኝነት እየናረ ሂዷል። ፈርጉሰን ከ27 ዓመታት በኃላ በጡረታ ከሥራ ሲገለሉ ዩናይትድ ከሊቨርፑል በላይ የአንግሊዝ ኃያሉ ክለብ መኾን ችሏል። ይሄ ለማንቼስተሩ ክለብ ደጋፊዎች ቅቤ እንደ መጠጣት ሲቆጠር፤ ለአንፊልዱ ክለብ ደጋፊዎች ደግሞ ህመም ኾኖባቸው ቆይቷል።

ሁለቱ ክለቦች 211 የጨዋታ ግንኙነት ታሪክ አላቸው። 82ቱ በዩናይትድ የበላይነት ተጠናቋል። ሊቨርፑል 71 ጨዋታዎችን አሸንፏል። በ58ቱ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል።

አሁን ላይ ሁለቱ ክለቦች የበላይነታቸውን በማንቸስተር ሲቲ ተነጥቀዋል። ማንቸስተር ዩናይትድም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየደከመ መምጣቱን ተከትሎ የሁለቱ ክለቦች ፍክክር አየፈዘዘ እንዲሄድ ምክንያት ኾኗል።

በ18ተኛ ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪሜር ሊግ ሁለቱ ክለቦች በአንፊልድ ይገናኛሉ። ሊቨርፑል በውድድር ዓመቱ ጥሩ ጉዞ እያደረገ ነው። ተጋጣሚው ዩናይትድ ግን በውጤት እጦት አየተፈተነ ነው።

ባለፈው ዓመት አንፊልድ ላይ በሰባት ግቦች አንገት የደፋው የቴንሃጉ ቡድን አሁንም ዋስትናው ጥያቄ ውስጥ ነው። ሊቨርፑል በቀላሉ ድል እንደሚቀናው ብዙዎች እየገመቱ ነው።ለዚህም ይመስላል ጨዋታው “በልኩ የማይገኘው የእንግሊዝ ታላቁ የእግር ኳስ ደርቢ” የሚል ስያሜ የተሰጠው።

በአስማማው አማረ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!”

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here