በ13ኛ ሳምንት የፕሪሜየር ሊጉ መርሐ ግብር መቻል ከሲዳማ ቡና ፤ ባሕር ዳር ከነማ ከአዳማ ከነማ ዛሬ ይጫወታሉ።

0
258

ባሕር ዳር፡ ጥር 25/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ዛሬ ከቀኑ 9:00 ሰዓት ሲዳማ ቡናን የሚገጥመው መቻል በውድድር ዓመቱ የተሸነፈው በአንድ ጨዋታ ብቻ ነው። ስምንት ጨዋታዎችን በማሸነፍ አሁን ላይ በ27 ነጥብ በደረጃ ሰንጠረዡ ሁለተኛ ነው።

መቻል የዛሬውን ካሸነፈ ነጥቡን ወደ 30 በማሳደግ የሊጉን መሪነት ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መረከብ የሚችሉበትን ዕድል መፍጠር ይችላል። በመቻል በኩል ባለፈው ሳምንት በቀይ ካርድ ከሜዳ ከተወገደው በኃይሉ ግርማ ውጪ ሁሉም የቡድኑ አባላት ለጨዋታው ዝግጁ ናቸው።

ከአሠልጣኝ ለውጥ በኃላ የተሻለ መነቃቃት ላይ የነበሩት እና ባለፈው የጨዋታ ሳምንት ግን ዳግም ሽንፈት ያስተናገዱት ሲዳማ ቡናዎች በአስራ አምስት ነጥቦች ዘጠነኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።

በመጨረሻ የሊግ ጨዋታቸው ምንም እንኳን የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ድርሻ ቢኖራቸውም የኳስ ቁጥጥራቸውን ወደ ግብ ዕድል ለመቀየር የተቸገሩት ሲዳማ ቡናዎች አሁንም ብልጭ ድርግም የሚለውን የቡድኑን የማጥቃት ጨዋታ ይበልጥ ማሻሻል ይኖርባቸዋል።

በሲዳማ ቡና በኩል ቅጣት ላይ የነበረው ጊትጋት ጉት ከቅጣት ሲመለስ ደስታ ደሙ ግን በጉዳት ከዛሬው ጨዋታ ውጭ ይኾናል። ሁለቱ ተጋጣሚዎች ከዚህ ቀደም 24 ጊዜ ሲገናኙ ሲዳማ 9 ጨዋታ በማሸነፍ ቀዳሚ ሲኾን መቻል 8 ጨዋታ አሸንፏል። 7 ጨዋታ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል።

ይህን ጨዋታ ኢንተርናሽናል ዳኛ ኤፍሬም ደበሌ በመሐል ዳኝነት ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ፋሲካ የኋላሸት እና የአማን ሞላ ረዳቶች መለሠ ንጉሴ በአራተኛ ዳኝነት ተሰይመዋል።
12 ሰዓት ላይ ባሕር ዳር ከነማ ከአዳማ ከተማ ይጫወታሉ።

ባሕር ዳር ከነማ በቀስታ ከዋንጫው ፉክክር እየራቀ ያለ ቡድን ነው ። ቡድኑ 19 ነጥብ ያለው ሲኾን ከሊጉ መሪ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ10 ነጥብ ርቆ ይገኛል። ደረጃውም ስድስተኛ ነው።

የጣና ሞገዶቹ በብዙ መልኩ ክፍተት ይታይባቸዋል። የአጥቂው ክፍል ትኩረት ማጣት፣ የተከላካዩ መዘናጋት እና የአማካዩ ክፍል ሜዳ ሙሉ አለመጫወት የቡድኑ ክፍተቶች ናቸው።
ከመስመር ወደ ግብ ቶሎ ቶሎ ኳስ ለመሻማት መቸገሩና ሲሻማም ፈጥኖ ወደ ግብ የመቀየር ውስንነት ቡድኑን የትልቅ ትንሽ አድርጎታል።

ዛሬ እነዚህን ውስንነቶች አርሞ ከገባ ብቻ ነው አዳማን መርታት አልያም ውጤት ተጋርቶ መውጣት የሚችለው። ባሕር ዳር ከነማ አለልኝ አዘነን እና ፍሬዘር ካሳን በአምስት ቢጫ ካርድ ሱሌይማን ትራኦሬን ደግሞ በጉዳት አይሰለፉም።

በከፍተኛ የውጤት ማጣት ቀውስ ውስጥ የሰነበቱት አዳማ ከተማዎች ባለፈው የጨዋታ ሳምንት ሀዋሳ ከተማን በመርታት እፎይታ ያገኙበትን ውጤት በማሳካት የነጥብ ብዛታቸውን ወደ 18 በማሳደግ ወደ ስምንተኛ ደረጃ ከፍ ብለዋል።

እንደ ባሕር ዳር ከነማ ሁሉ በማጥቃቱ ረገድ ግቦችን ለማግኘት ተቸግረው ነው የሰነበቱት።በአዳማ በኩል አቡበከር ሻሚል፣ ሀይደር ሸረፋ ፣ አሕመድ ረሺድ ፣ ተክለማርያም ሻንቆ ፣ ሐቢብ መሐመድ ፣ መላኩ ኤልያስ እና ቻርለስ ሪቫኑ በክፍያ ጥያቄ ምክንያት ከክለቡ ጋር የማይገኙ መኾናቸው እየተነገረ ነው።

ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም ስምንት ጊዜ ተገናኝተዋል። ባሕር ዳር በስድስቱ በማሸነፍ የበላይነት አለው። አዳማ አንድ አሸንፎ አንዱን አቻ ተለያይቷል። የምሽቱን መርሐ ግብር በዋና ዳኝነት ኢንተርናሽናል ዳኛ በላይ ታደሠ ሲመራው ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ትግል ግዛው እና ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ወጋየሁ ዘውዱ ረዳቶች ናቸው። ኢንተርናሽናል ዳኛ አሸብር ሰቦቃ በአራተኛ ዳኝነት ተመድቧል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here