ሰሜን ለንደን ደርቢን ማን በድል ይወጣል?

0
7

ባሕር ዳር: ኅዳር 13/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የእንግሊዝ ፕሪምዬር ሊግ በ12ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ ይመለሳል። በ12ኛ ሳምንት ተጠባቂ ከኾኑ ጨዋታዎች ውስጥ በሰሜን ለንደን ደርቢ አርሰናል ከቶተንሃም ሆትስፐር በኤምሬትስ የሚያደርጉት ፍልሚያ ነው። ይኼው ተጠባቂ ጨዋታ እሁድ ምሽት 1፡30 ላይ ይካሄዳል።

አርሰናል እና ቶተንሃም ሆትስፐር ከዚህ በፊት ካደረጓቸው ጨዋታዎች ውስጥ አርሰናል 84 ጊዜ ሲያሸንፍ፣ ቶተንሃም 61 አሸንፏል፡፡ 52 ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት የተጠናቀቁ ናቸው፡፡

አርሰናል በ2025/26 የእንግሊዝ ፕሪምዬር ሊግ በ11 ጨዋታዎች 26 ነጥቦችን በመያዝ ሊጉን እየመራ ነው። ቶተንሃም ደግሞ በ11 ጨዋታዎች 18 ነጥቦችን ሠብሥቦ 5ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ሁለቱ ክለቦች በርካታ ተጫዋቾችን በጉዳት ምክንያት በእሁዱ ጨዋታ የማያሰልፉ መኾናቸውን ቢቢሲ ስፖርት በገጹ አስነብቧል፡፡ በቶተንሃም በኩል 13 ተጨዋቾች የሰሜን ለንደን ደርቢ እንደሚያመልጣቸው መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

ጀምስ ማዲሰን፣ ዴጃን ኩልሴቭስኪ፣ ዶሚኒክ ሶላንኬ፣ ቤን ዴቪስ፣ ቢሱማ፣ አርኪ ግሬይ፣ ራንዳል ኮሎሙዋኒ እና ሌሎችንም ለደርቢው ጨዋታ አይደርሱም።

ለአርሰናል ደግሞ ጋብሬል ጄሱስ፣ ካይ ሀቨርትዝ፣ ኖኒ ማዱኬ፣ ጋብሬል ማጋሌሽ፣ ማርቲን ኦዲጋርድ፣ ጋብሬል ማርቲኔሊ እና ቪክቶር ዮኮሬሽ ለጨዋታው እንደማይደርሱለት ተዘግቧል፡፡

አርሰናል እና ቶተንሃም በመጨረሻ ካደረጓቸው ስድስት ጨዋታዎች ውስጥ አርሰናል አምስቱን በማሸነፍ የበላይ ነው። አርሰናል በሜዳው ከቶተንሃም ጋር ባደረጋቸው 32 ጨዋታዎች የተሸነፈው በአንዱ ብቻ ነው፡፡

የቶተንሃሙ አሠልጣኝ ቶማስ ፍራንክ ቶተንሃምን እያሠለጠኑ የመጀመሪያ የሰሜን ለንደን ደርቢ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ፡፡

ዛሬ ከኒውካስል ዩናይትድ ጋር የሚፋለሙት የፔፕ ጋርዲዮላዎቹ ማንቸስተር ሲቲዎች ጨዋታቸውን በአሸናፊነት ከተወጡ ከአርሰናል ጋር የሚኖራቸውን የነጥብ ልዩነት ወደ አንድ በማጥበብ በአርሰናል ላይ ጫና ይፈጥራሉ።

የሰሜን ለንደኑን የደርቢ ጨዋታ በመኸል ዳኝነት ማይክል ኦሊቨር እንደሚመሩትም ታውቋል፡፡

ከዚህ ጨዋታ በተጨማሪ ዛሬ በርንሌይ ከቼልሲ፣ ዎልቭስ ከክሪስታል ፓላስ፣ ሊቨርፑል ከኖቲንግሃም ፎረስት፣ ፉልሃም ከሰንደርላንድ፣ ብራይተን ከብሬንትፎርድ፣ በርንማውዝ ከዌስትሃም ጋር ተጠባቂ ጨዋታዎችን ያደርጋሉ፡፡


እሁድ ከአርሰናል ከቶተንሃም ጨዋታ በተጨማሪ ሊድስ ዩናይትድ ከአስቶንቪላ የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል።

የ12ኛው ሳምንት የማሳረጊያ ጨዋታ ደግሞ ሰኞ ምሽት ማንቸስተር ዩናይትድ ከኤቨርተን የሚያደርጉት ፍልሚያ ነው።

ዘጋቢ፡- እሱባለው ይርጋ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here