የቀዮቹ እና ነጮቹ ቀጠሮ በአንፊልድ

0
13

ባሕር ዳር: ጥቅምት 25/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ የስድስት ጊዜ ባለድሉ ሊቨርፑል የ15 ጊዜ አሸናፊውን ሪያል ማድሪድን ምሽት በአንፊልድ ያስተናግዳል።

ሊቨርፑሎች ዘንድሮ አጀማመራቸው እንዳለፉት ዓመታት ጠንካራ አይደለም። በእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግም በተከታታይ ሽንፈት ደርሶባቸዋል። ነገር ግን በሳምንቱ መጨረሻ ወደ ድል ተመልሰዋል።

ዛሬ አስቶን ቪላ ላይ ያገኙትን አሸናፊነት ለማስቀጠል ከሪያል ማድሪድ ጋር ይፋለማሉ። ሊቨርፑሎች ከስፔን ቡድኖች ጋር ባደረጉት ያለፉ 15 ጨዋታዎች በሁለቱ ብቻ መሸነፋቸውን ታሪክ ያስረዳል።

ከሊቨርፑል በተቃራኒ ሪያል ማድሪድ በስፔን ላሊጋ የስኬት ጉዞ ላይ ነው። ላሊጋውን በ30 ነጥብ እየመራ ሲኾን በሻምፒየንስ ሊግም ትልልቅ ቡድኖችን ማሸነፍ የቻለ ክለብ ነው።

የቡድኑ ያለመሸነፍ ግስጋሴ፣ የተጫዋቾች ጉጉት እና መነሳሳት፣ የድል ጥማት እና የቡድን ስሜት የአሎንሶው ቡድን የእስካሁን ጉዞው መገለጫ ነው።

የኪሊያን ምባፔ፣ የቪኒሺየስ እና የቤሊንግሃም ጥምረት፣ የድል ጉጉት እና ወደ ግብ አስቆጣሪነት መመለስ በድምሩም የሎስ ብላንኮዎቹ ያለፉት ጨዋታዎች ድልና መነሳሳት የአሸናፊነቱን ቅድመ ግምት አሰጥቷቸዋል፡፡

ሁለቱ ቡድኖች በመድረኩ 12 ጊዜ የመገናኘት ታሪክ አላቸው። ማድሪድ ሰባት ጊዜ፣ ሊቨርፑል አራት ጊዜ ሲያሸንፉ አንድ ጊዜ ደግሞ አቻ መለያየታቸውን ቢቢሲ ስፖርት አስነብቧል።

የጨዋታው ሌላ ተጠባቂ መልክ ሊቨርፑሎች ለባለውለታቸው እና ዛሬ ግን በተቃራኒ ለሚገጥማቸው ለትሬንት አሌክሳንደር አርኖልድ የሚያሳዩት ምላሽ ነው፡፡

በሊቨርፑል ስኬታማ ጊዜን ያሳለፈው የቀኝ መስመር ተከላካዩ አርኖልድ ሌላ ክለብ መፈለጉ ለመርሲሳይዶች ምቾት አልሰጠም።

አርኖልድ ለሊቨርፑል የመጨረሻ ጨዋታ ባደረገበት አጋጣማ የአንፊልድ ታዳሚዎች የተቃውሞ ድምጽ ማሰማታቸውን ኢንዲፔንደንት አስታውሷል።

ዛሬስ መርሲሳይዶች ሪያል ማድሪድን ወክሎ የሚሰለፈው አርኖልድን ኳስ በያዘ ቁጥር እየጮሁ ይቃወሙታል ወይስ ለውለታው ክብር ይሰጡታል? የሚለው ሌላው የምሽቱ የአንፊልድ ቀጠሮ ማሞቂያ ነው።

ዘጋቢ፦ ዋሴ ባየ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here