ከወርቆቹ መካከል አንዷ…

0
71

ባሕር ዳር: ጥቅምት 22/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የጽናት መለያ፣ የወርቅ ዘመን አንበሳ፣ የሀገር ፍቅር ማደሪያ፣ የቁርጠኝነት፣ የብርታት እና የአልሸነፍ ባይነት ምሽግ ናት አትሌት መሠረት ደፋር።

በ3 ሺህ ሜትር፣ በ5 ሺህ ሜትር እና የሁለት ማይል የቤት ውስጥ ሩጫ ውድድሮች ላይ በአስደናቂ ብቃት የተወዳደረች ኢትዮጵያዊ የረጅም ርቀት ሯጭ ናት።

በዚህም ዓለም አቀፍ ክብረ ወሰኖችን ሰባብራለች፤ የሀገሯን ሰንደቅ ከፍ አድርጋ እርሷም ከፍ ብላለች።

መሠረት ቤተሰቦቿ በኢኮኖሚ አቅማቸው ዝቅተኛ ስለነበሩ በልጅነት ዕድሜዋ ከትምህርቷ ጎን ለጎን የተለያዩ ሥራዎችን እየሠራች ነው ያደገችው። ይህ ለችግሮች እጅ ያለመስጠት ብርታት አሁን ላይ በእርሷ መንገድ እያለፉ ላሉ ታዳጊዎች አስተማሪ ተሞክሮ ነው።

መሠረት ወደ ሩጫ ያዘነበለችው የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ እያለች እንደነበር ታሪኳ ያሳያል። አጋጣሚውም በትምህርት ሚኒስቴር አማካኝነት ይካሄድ የነበረ የሩጫ ውድድር ላይ ማሸነፏ ነው። በዚህም የባንኮች አትሌቲክስ ቡድንን ተቀላቅላለች።

ከቡድኑ ጋር በነበራት ቆይታ በርካታ የሀገር ውስጥ ውድድሮች ላይ ባሳየችው የአሸናፊነት ድል ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እንድትመረጥ አስችሏታል።

መሠረት ለመጀመሪያ ጊዜ እ.ኤ.አ. በ2004 በአቴንስ ኦሎምፒክ የ5ሺ ሜትር ውድድር ለመወዳደር የተጠባባቂነት ዕድል አግኝታለች። በመጨረሻ የመወዳደር እድል አግኝታ ውድድሩሩ በአስደናቂ ብቃት አሸንፋለች።

ተጠባባቂ የነበረችው መሰረት የወርቅ ሜዳሊያ በማግኘት የሀገሯን ባንዲራ ከፍ አድርጋ የድል ማማ ላይ መስቀል ቻለች። ይህንኑ ብቃቷን በ2ዐ12 እ.ኤ.አ ለንደን ኦሎምፒክ ላይ ደግማዋለች።

ብዙ ዓለም አቀፍ ውድድሮችን አሸንፋለች። የዓለም ክብረ ወሰኖችንም አሻሽላ አስመዝግባለች። ካሻሻለቻቸው የዓለም ክብረ ወሰኖች ውስጥ እ.ኤ.አ. በ2006 ኒውዮርክ ላይ የተካሄደው የ5ሺ ሜትር የሩጫ ውድድር አንዱ ነው። በ2007 ጀርመን ላይ የተካሄደው የ3ሺህ ሜትር የቤት ውስጥ ውድድር ደግሞ ሌላኛው ነው።

በዚሁ እ.ኤ.አ በ2007 ካሊፎርኒያ ላይ እና ቤልጂየም ላይ የተካሄዱት የሁለት ማይል ውድድሮች ተጠቃሾች ናቸው። በዚህ ውጤቷም የዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን “እ.ኤ.አ የ2ዐዐ7 ምርጥ አትሌት ሽልማት ማሸነፏን የዓለም አትሌቲክስ መረጃ ያሳያል።

ጥቅምት 02/2018 ዓ.ም በተካሄደው የዘንድሮው አምስተኛው የአፍሪካ ኢምፓክት አዋርድም በአትሌቲክስ ዘርፍ ተሸላሚ ኾናለች፡፡ የአፍሪካ ኢምፓክት አዋርድ በየዓመቱ ከስፖርት፣ ከኪነ ጥበብ፣ ከቢዝነስ ዘርፍ ተመርጠው ላደረጉት በጎ አስተዋጽኦ እና ስኬት ሽልማት እና እውቅና የሚሰጥበት መድረክ ነው።

በእውቅና እና ሽልማት መርሐ ግብሩ ተገኝታ ለወጣት እና ታዳጊ አትሌቶች እንዲኹም በተለየ ሙያ ዘርፍ ተሠማርተው ለሚገኙ ወጣቶች መልዕክት አስተላልፋ ነበር፡፡

በዚህም መጠንከር፣ መሥራት እና በጽናት መገኘት ለትልቅ ሽልማት እና ቦታ እንደሚያበቃ ነው የጠቀሰችው፡፡

አሁን ላይ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዝዳንት ኾና እየሠራች ነው እንቁዋ አትሌት።

የኢትዮጵያ አትሌቶች ማኅበር ፕሬዝዳንት እና የኢትዮጵያ አትሌቶች ፌዴሬሽን ሥራ አሥፈጻሚ አባል አትሌት የማነ ጸጋዬን አሚኮ ስለ መሠረት እማኝነት ጠይቆታል።

የሩጫ ልምምድ እና ውድድር ላይ አልሸነፍ ባይ እና በጣም ጠንካራ፣ ሴት አትሌቶችን ማበረታታት እና ትልቅ ደረጃ እንዲደርሱ የማድረግ ጥረት አንዱ መገለጫዋ ነው ብሏታል።

ምንም እንኳ የሁሉም አትሌቶች ሀገር ወዳድነት ፍቅር የአደባባይ ሀቅ ቢኾንም መሠረት ያላት ሀገር ወዳድነት የሚለይ ይመስለኛል አለን። በማሳያነትም መሪ ከኾነች በኋላ በቅርቡ ቶኪዮ ላይ የነበረ የሩጫ ውድድር ላይ የተፈጠረን አጋጣሚ አንስቷል።

ኢትዮጵያ ውጤት የተጠበቀውን ውጤት ባለማስመዝገቧ በእጅጉ ማዘኗን እና መጎዳቷን ጠቅሷል። ምንም እንኳ ታዳጊዎች ላይ ባለመሠራቱ እና አትሌቲክስ ላይ ያሉ ክፍተቶች ይዘውት የመጡት ችግር ቢኾንም ለእርሷ ከባድ ኾኖባታል ነው ያለን።

አሁን ባላት የመሪነት ተግባርም ከሌሎች ሥራ አሥፈጻሚዎች ጋር በመኾን ውጤት የራቀውን አትሌቲክስ ለመመለስ በታታሪነት እየሠራች መኾኑን መስክሯል።

መሠረት ጥሩ የማኅበራዊ ግንኙነት ተሳትፎ አላቸው ከሚባሉ አትሌቶች አንዷ እንደኾነችም ጠቅሷል። የተለያዩ የበጎ አድራጎት ሥራዎች ላይ ተሳትፎ ማድረግ የመሲ መገለጫዎች ናቸውም ብሏል።

ከአትሌት መሠረት ደፋር የድል ቁርጠኝነት፣ የአዕምሮ ዝግጁነት፣ ጥንካሬ እና ትኩረት፣ የሥነ ልቦና ጥንካሬ፣ የሀገር ፍቅር እና ክብር፣ ትህትና እና የትውልድ ሽግግር ታሪኳ ለዛሬው እና ለነገው ተተኪ ትውልድ በገንዘብ የማይገመት ትምህርት እና መነሳሳት ይሰጣል።

መሲ እንደ አበበ ቢቂላ የመሆን ህልሟን ኑራ፣ ለሀገር ኩራት ለተተኪዎችም አርዓያ ሆናለች። ሀገሯን እና ራሷን ከፍ ባደረገችበት አትሌቲክስ ዛሬም በሌላ ኅላፊነት ላይ ትተጋለች። መሲ “ከወርቆች መካከል አንዷ”።

ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here