ደብረማርቆስ: ጥቅምት 20/2018 ዓ.ም (አሚኮ) 31ኛው የምሥራቅ ጎጃም ዞን ሀገር አቋራጭ ውድድር በደብረ ማርቆስ ከተማ ተካሂዷል።
የምሥራቅ ጎጃም ዞን ወጣቶች እና ስፖርት መምሪያ ኀላፊ ቢሻው ሞላ በዞኑ ባለፉት ሁለት ዓመታት ባጋመው የሰላም ዕጦት ምክንያት ተቀዛቅዞ የቆየውን የስፖርት ዘርፍ ለማነቃቃት እና በቀጣይ በክልል ደረጃ ለሚካሄደው ሀገር አቋራጭ ውድድር ዞኑን የሚወክሉ ስፖርተኞችን ለመምረጥ ታልሞ ውድድሩ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።
ስፖርት ለሰላም ትልቅ አበርክቶ እንዳለው የተናገሩት ኀላፊው የበጋ ሥልጠና እና ውድድር ሥራዎች ላይ በትኩረት እየተሠራ መኾኑንም ተናግረዋል።
የምሥራቅ ጎጃም ዞን አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ሚካኤል ስዩም ውድድሩ አቅምን ከመፈተሽ ባለፈ ለክልል፣ ለሀገር ተተኪ እና ተወዳዳሪ አትሌቶችን ለማፍራት ጉልህ ፋይዳ እንዳለው አንስተዋል።
ስፖርት ማኅበራዊ መስተጋብርን ከማሳደጉ በተጨማሪ ለሰላም ያለው ፋይዳ የማይተካ መኾኑንም አስገንዝበዋል፡፡
የውድድሩ ተሳታፊ አትሌቶችም በቅርቡ በክልል ደረጃ በሚካሄደው ሀገር አቋራጭ ውድድር የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ እንደሚተጉ ተናግረዋል።
የሀገራቸውን ስም የማስጠራት ትልቅ ዓላማ ይዘው እየሠሩ መኾናቸውንም ገልጸዋል።
በ31ኛው የምሥራቅ ጎጃም ዞን ሀገር አቋራጭ ውድድር በሁለቱም ጾታዎች በተለያዩ ርቀቶች ጥሩ ሰዓት ያስመዘገቡ አትሌቶች በክልል ደረጃ በሚካሄደው ሀገር አቋራጭ ውድድር ላይ ተሳታፊ እንደሚኾኑም ተመላክቷል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!



