31ኛው ዞናዊ ሀገር አቋራጭ የሩጫ ውድድር በፍኖተሰላም ከተማ ተካሄደ።

0
8
ፍኖተሰላም: ጥቅምት 18/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በምዕራብ ጎጃም ዞን 31ኛው ዞናዊ ሀገር አቋራጭ የሩጫ ውድድር በፍኖተሰላም ከተማ ተካሂዷል።
”ስፖርት ለሰላም ፣ ለዘላቂ ዕድገት እና ልማት ግብ” በሚል መሪ መልዕክት በ6ሺህ፣ በ8ሺህ እና 10 ሺህ ሜትር አዋቂዎች የሩጫ ውድድር ነው የተካሄደው።
የምዕራብ ጎጃም ዞን ተወካይ አሥተዳዳሪ እና የሰላም እና ጸጥታ መምሪያ ኀላፊ ሙሉጌታ ዓለም ዞኑ በርካታ ስፖርተኞች የሚወጡበት አካባቢ ቢኾንም በሰላም እጦቱ ምክንያት ውድድሮች ተቋርጠው መቆየታቸውን ተናግረዋል።
ውድድሩ እንደ ሀገር ተወዳዳሪ ስፖርተኞችን በማፍራት የሥራ ዕድልም እንደሚፈጥር ጠቁመዋል።
ስፖርታዊ ውድድሮችን ለማካሄድ ሰላም በእጅጉ ስለሚያስፈልግ ለሰላም መሥራት እንደሚገባም ነው ያስረዱት።
ውድድሩ ለክልላዊ ውድድሮች አትሌቶችን ለመመልመል ዓላማ ያደረገ መኾኑን የምዕራብ ጎጃም ዞን የወጣቶች እና ስፖርት መምሪያ ኀላፊ በዕውቀቱ ተሾመ ተናግረዋል።
ውድድሩ በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት ተቀዛቅዞ የቆየውን የስፖርት ዘርፍ በማነቃቃት ወጣቶች ለሰላም እና ልማት የበኩላቸውን እንዲወጡ ሚናው የጎላ መኾኑን ጠቁመዋል።
ቀጣይም ሃብት በማሠባሠብ በ17 የውድድር አይነቶች ለክልል እና ለሀገር አቀፍ ስፖርተኞችን ለማፍራት እየተሠራ መኾኑን አንስተዋል።
የፍኖተሰላም ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ጊዜው ደግአረገ በከተማ አሥተዳደሩ አሁን ላይ የሰላም ሁኔታው እየተረጋጋ መኾኑን ተናግረዋል። በዚህም ስፖርታዊ ውድድሮች መካሄዳቸውን ገልጸዋል።
የውድድሩ ተሳታፊዎች ውድድሮች በመካሄዳቸው ደስተኛ መኾናቸውን እና ለሌሎች ውድድሮች ራሳቸውን ለማዘጋጀት እንደሚሠሩ ገልጸዋል።
በውድድሩ ከአንድ እስከ ሦሥት ለወጡ አትሌቶች የሜዳልያ እና ዋንጫ ሽልማት ተሰጥቷል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here