ባሕር ዳር: ጥቅምት 16/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ዛሬ አምስት ጨዋታዎች ይካሄዳሉ። ምንአልባትም የዛሬ ጨዋታዎች በውድድሩ ያለውን ፉክክር ከማጠናከር በዘዘለለ የደረጃ ለውጥም ሊያስከትሉ ይችላሉ።
ከዛሬ ተጠባቂ ጨዋታዎች መካከል በሊጉ የደረጃ ሠንጠረዥ እና እስካሁን ባደረጋቸው ጨዋታዎች ስኬታማ እየኾነ የመጣው አርሰናል በሜዳው ክርስታል ፓላስን የሚያስተናግድበት ጨዋታ ተጠባቂ ነው።
ሁለቱ ክለቦች እስካሁን 51 ጊዜ ተገናኝተዋል። አርሰናል 31 ጊዜ በማሸነፍ የበላይነት ያለው ሲኾን ክርስታል ፓላስም አምስት ጊዜ ማሸነፍ ችሏል። ሁለቱ ክለቦች እስካሁን ባደረጓቸው ጨዋታዎች አቻ መለያየት የቻሉትም 15 ጊዜ ነው።
በ19 ነጥብ የደረጃ ሠንጠረዡ አናት ላይ የሚገኘው አርሰናል እስካሁን 15 ኳሶችን ከመረብ ጋር በማገናኘት የተሻለ አቋም እንዳለው እያስመሰከረ ያለ ክለብም ነው።
በተመሳሳይም ክርስታል ፓላስ በ13 ነጥብ በደረጃ ሠንጠረዡ ዘጠነኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ሲኾን 13 ኳሶችን ከመረብ በማሳረፍ የማይተናነስ ቡድን እንደኾነ ቁጥሮች ያሳያሉ።
አርሰናል በሜዳው የሚጫዎት በመኾኑ እና ከዚህ በፊት ባደረጋቸው ጨዋታዎች የመሸነፍ ታሪክ ስለሌለው ዛሬ የማሸነፍ ቅድመ ግምትን አግኝቷል። ጨዋታውም 10፡00 ይካሄዳል።
በሌላ በኩል በደረጃ ሠንጠረዡ በ16 ነጥብ ሦስተኛ ጀረጃ ላይ የተቀመጠው ማንቸስተር ሲቲ ዛሬ በ12 ነጥብ 12ኛ ደረጃ ላይ ከሚገኘው አስቶንቪላ የሚያደርገው ጨዋታ ተጠባቂ ነው።
ሲቲ ይህን ጨዋታ ማሸነፍ ከቻለ በሊጉ ደረጃውን ከፍ ማድረግ ይችላል። ለውጥ ከማስከተሉም በላይ የተሻለ ፉክክር በሊጉ እንዲኖር ያስችላል።
ሁለቱ ክለቦች በታሪክ 166 ጊዜ ተገናኝተዋል። 75 ጊዜ የማሸነፍ የበላይነት ያለው ሲቲ ሲኾን አስቶንቪላ በ51 አጋጣሚ የበላይ ሆኗል። በቀሪ ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርተዋል።
ሲቲ ከሜዳው ውጭ የሚጫዎት በመኾኑ እና እስካሁን ባላቸው ታሪክ አስቶንቪላ በሜዳው ሲቲን በተደጋጋሚ ያሸነፈው በመኾኑ የዛሬውን ጨዋታ ተጠባቂ አድርጎታል። ጨዋታው 10፡00 ላይ ይጀምራል።
በርን ማውዝ ከከኖቲንግሃም ፎረስት እና ወልቨስ ከበርንለይ በተመሳሳይ ሰዓት 10፡00 ይጫወታሉ። የኤቨርተን እና ቶትንሃም ጨዋታ ደግሞ 12፡30 ላይ ይጀምራል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!



