የሊቨርፑል ችግር ምንድን ነው?

0
9
ባሕር ዳር: ጥቅምት 10/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ሊቨርፑል በጨዋታ አንድ ነጥብ እንኳ ማግኘት ከተሳነው አራት ጨዋታዎች ተቆጠሩ። አራት ተከታታይ ሽንፈቶችን በማስተናገድ ቡድኑ የውጤት ቀውስ ውስጥ ይገኛል።
አሠልጣኙ አርኔ ስሎት በአሠልጣኝነት ዘመናቸው በተከታታይ አራት ጨዋታ የተሸነፉበት አስቸጋሪ ጊዜ ላይም ተገኝተዋል። ሰውየው ባለፈው ዓመት ክለቡን ተረክበው የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ አንስተዋል። በአንፊልድም ብዙ አድናቆት ተችሯቸዋል።
የ2025/26 የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግን የማሸነፍ ቅድመ ግምት ያገኘው ሊቨርፑል ነው። በእርግጥ አሁንም መጀመሪያ ከተሰጠው ግምት ዝቅ ይል ካልኾነ በስተቀር የሊቨርፑል የዋንጫ ጉዞን ጥያቄ ውስጥ ማስገባት ጊዜው የቀደመ ይኾናል። ፕሪምየር ሊጉ ገና ስምንተኛ ሳምንቱ ላይ መገኘቱ አይረሳምና።
ነገር ግን በቅርብ አራት ጨዋታዎች ያሳየው ደካማ አቋም አሳሳቢ ነው። ተከታታይ አራት ሽንፈት ያስተናገደው የአርኔ ስሎቱ ቡድን ሦሥቱ በፕሪምየር ሊጉ የገጠሙት ሽንፈቶች ናቸው።
ይህን ተከትሎ ከፕሪምየር ሊጉ መሪ አርሰናል ጋር ያለው የነጥብ ልዩነት አራት ደርሷል። ገና በሊጉ የስምንተኛ ሳምንት ጉዞም ሦስት ሽንፈቶችን አስተናግዷል።
በተሸነፈባቸው አራት ጨዋታዎች ስድስት ግቦች ሲቆጠሩበት፣ ያስቆጠረው አራት ነው። እኝህ ሁሉ ነገሮች ለጊዜውም ቢኾን በሊቨርፑል ቤት መሰፋት ያለበት ቀዳዳ እንዳለ ያሳያሉ።
የስካይ ስፖርት ተንታኙ ጅሚ ካራገር የሊቨርፑል መሠረታዊ ችግር የመከላከል ብቃት ማነስ መኾኑን ጠቁሟል። ይህን ችግር ቶሎ ካላስተካከለም አርሰናልና ሲቲ በጊዜ ርቀውት እንዳይጓዙ ስጋቱን አንስቷል።
ከማንቸስተር ዩናይትዱ የ2ለ1 ሽንፈት በኋላ ስለቡድናቸው ሃሳብ የሰጡት አሠልጣኙ አርኔ ስሎት ቡድናቸው ጨዋታውን ለማሸነፍ በቂ ዕድሎች መፍጠሩን አንስተዋል። ነገር ግን መከላከል ላይ በተለይ የአየር ላይ ኳስ የመከላከል ችግርን በአጽንኦት አንስተዋል።
የሊቨርፑል የተከላካይ ክፍል በድሮው ጥንካሬው ላይ አለመገኙቱ የሽንፈቶቹ መደጋገም ማሳያ ነው። ቨርጅል ቫንዳይክ እና ኢብራሂማ ኮናቴ በሚታወቁበት ብቃት ላይ አይገኙም።
በተጨማሪም ሊቨርፑል በክረምቱ ያስፈረማቸው የመስመር ተከላካዮች አጫጭር መኾን ቡድኑ በአየር ላይ መከላከል እንዲጠቃ አድርጎታል ይላል የቀድሞው የቀዮቹ ተጫዋች ጋራገር።
ሊቨርፑል የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ባነሳበት ያለፈው ዓመት በመስመር ተከላካይ አርኖልድን እና ሮበርትሰንን ይጠቀም ነበር። በዚህ የውድድር ዓመት ወደ ሪያል ማድሪድ ያመራው አርኖልድን በፍሪንፖንግ ሲተካ፣ ሮበርትሰንም ከበርንማውዝ አንፊልድ በደረሰው ኬርኬዝ ወደ ተጠባባቂ ወንበር ወርዷል።
በተጨማሪም የሊቨርፑል ያለፉት ዓመታት ወሳኝ ተጫዋች መሐመድ ሳላህ በሚታወቅበት አቋም አለመገኘት የሊቨርፑልን ወቅታዊ ችግር አባብሶታል ባዮች ጥቂት አይደሉም።
የቡድኑ አዳዲስ ፈራሚዎች በደንብ ከቡድኑ ጋር አለመዋሃድም ሌላ ተጠቃሽ ምክኒያት ነው።
ዘጋቢ፦ አስማማው አማረ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here