ደባርቅ፡ መስከረም ፡ 21/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ለኢንስትራክተር እንዳልክ ቀለመወርቅ አትሌቲክስ ማሠልጠኛ ማዕከል የገንዘብ እና የስፖርት ትጥቅ ድጋፍ አድርጓል።
በሰሜን ጎንደር ዞን ዳባት ወረዳ የሚገኘው የኢንስትራክተር እንዳልክ ቀለመ ወርቅ የአትሌቲክስ ማሠልጠኛ ማዕከል በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ሙሉ ዕውቅና አግኝቶ ወደ ሥራ የገባው በኅዳር ወር 2017 ዓ.ም ነው።
የኢትዮጵያ ስፖርት ፌዴሬሽን ከሁለት ሚሊዮን ብር በላይ የገንዘብ ድጋፍ እና ለ30 ሠልጣኞች እና አሠልጣኞች ሙሉ የስፖርት ትጥቅ ድጋፍ አድርጓል።
የዳባት ወረዳ ዋና አሥተዳዳሪ መርሻ ወረታ የአትሌቲከስ ማዕከሉን በዘላቂነት ለማሻሻል እና ለመደገፍ የተለያዩ ተግባራትን እያከናዎኑ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
ማዕከሉ በኅብረተሰቡ መልካም ፈቃድ እና ተነሳሽነት የተገነባ በመኾኑ ማዕከሉን ለመደገፍ በሚደረገው ጥረት ማኅበረሰቡ በንቃት እየተሳተፈ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ማዕከሉ ከአካባቢው ማኅበረሰብ ባለፈ እንደ ክልል ብሎም እንደ ሀገር ፋይዳው የጎላ ነው ብለዋል።
ስለኾነም ማዕከሉን ለማሳደግ እና በዘላቂነት ለማሻሻል በሚደረገው ጥረት ሁሉም ባለድርሻ አካል የበኩሉን ሊወጣ ይገባል ነው ያሉት።
የዳባት ወረዳ ስፖርት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ የሽበር ቢራራ ማዕከሉ በአጭር ጊዜ ውስጥ የተለያዩ አበረታች ለወጦች ማምጣቱን ገልጸዋል።
የአሠልጣኝ ምደባ እና የአትሌት ምልመላ ተካሂዶ በሙሉ አቅም ወደ ሥራ መግባታቸውንም አብራርተዋል።
ያሉ የስፖርት ትጥቅ እና ሌሎች የስፖርት ቁሳቁሶች እጥረት ለመቅረፍ ከተቋማት እና ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር በቅርበት እየተሠራ ነው ብለዋል።
ማዕከሉ አካባቢያዊም ኾነ ሀገራዊ ፋይዳው ጉልህ በመኾኑ በጎ ፈቃደኞች ድጋፍ ሊያደርጉ እንደሚገባም ገልጸዋል።
የማዕከሉ አሠልጣኝ ዘመነ የኔዓለም በበኩላቸው እየተደረጉ ያሉ ድጋፎች የስፖርተኞችን ችግር ለመቅረፍ እንደሚያስችሉ አብራርተዋል።
ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት ቅድሚያ ምቹ ሁኔታን መፍጠር ተገቢ መኾኑንም አንስተዋል።
ለማዕከሉ የተሰጠው ትኩረት እና ልዩ ልዩ ድጋፎች የአትሌቶቹን ሥነ-ልቦና ለማነቃቃት እንደሚያግዙም ገልጸዋል።
ሠልጣኝ አትሌቶችም የስፖርት ቁሳቁስ ባለመሟላታቸው አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ማለፋቸውን አብራርተዋል።
እየተደረጉ ያሉ ድጋፎች ጥሩ ውጤት ለማምጣት ለሚያደርጉት ጥረት አጋዥ መኾኑንም ነው የተናገሩት።
በሚደረገው ድጋፍ ልክ ዕድገት ማሳየት እና ውጤት ማምጣት እንደሚጠበቅባቸውም ገልጸዋል።
በቀጣይም ማዕከሉን እና ተተኪ ስፖርተኞችን ለመደገፍ የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!