ኅብረተሰቡ የጤና እና የአካል ብቃት እንቅስቃሴን ባሕል ማድረግ አለበት።

0
13
ደብረ ማርቆስ፡ መስከረም 20/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ወጣቶች እና ስፖርት መምሪያ ከአማራ ክልል ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ ጋር በመተባበር ለ13 ቀናት ሲሰጥ የቆየውን የ1ኛ ደረጃ የአካል ብቃት የአሠልጣኞች ሥልጠናን አጠናቅቋል፡፡
የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ወጣቶች እና ስፖርት መምሪያ ኀላፊ ተስፋዬ አዕምሮ በከተማዋ የሚገኙ የስፖርት አሠልጣኞች በዕውቀት እና በክህሎት ታግዘው ሳይንሳዊ በኾነ መንገድ ሥልጠናዎችን እንዲሰጡ ለማስቻል ታልሞ ሥልጠናው ስለመሰጠቱ ተናግረዋል፡፡
የአሠልጣኞች ሥልጠናን የተከታተሉ የስፖርት ባለሙያዎች በከተማው በሚገኙ ስፖርት ቤቶች የከተማውን ማኅበረሰብ የማገልገል እና ጤናማ ማኅበረሰብ የመፍጠር ኀላፊነት እንዳለባቸውም ጠቁመዋል፡፡
ለሠልጣኞች ሥልጠና ሲሰጥ አሚኮ ያገኘው ማስተር ሀብታሙ ጥላሁን በከተማዋ ለሚገኙ አሠልጣኞች የ1ኛ ደረጃ የጤና እና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ሥልጠና መሰጠቱ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች እንዳሉት ተናግሯል፡፡
ጠንካራ፣ ውጤታማ እና ጤናማ ማኅበረሰብ ለመፍጠር ሥልጠናው የጎላ ፋይዳ እንዳለው አመላክቷል፡፡ አሠልጣኞች በስፖርት ማዕከላት ሥልጠናዎችን ሲሰጡ ተላላፊ ያልኾኑ እንደ ግፊት እና ስኳር የመሳሰሉትን በሽታዎች ከመከላከል ባሻገር የማኅበረሰብ ስፖርት እንዲስፋፋ ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋልም ብሏል፡፡
ለአሚኮ አስተያየታቸውን ከሰጡ ሠልጣኞች መካከል ወጣት ሳቦም ገበያው እና ወጣት ጌትነት አያሌው ሥልጠናው ኅብረተሰቡ ስፖርትን ባሕል እንዲያደርግ ያስችላል ብለዋል።
ሥልጠናው ሳይንሱን ያልተከተለ እና በዘልማድ የሚደረግ የጤናና የአካል ብቃት እንቅስቃሴን ለማስቀረት እንዲሁም በሽታን አስቀድሞ ለመከላከል ያግዛል ነው ያሉት።
በተለያዩ ችግሮች የተቀዛቀዘውን ስፖርት ለማነቃቃትም የሚያስችሉ ግብዓቶች የተወሰዱበት ሥራ እንደኾነ በመድረኩ ተገልጿል።
በሥልጠናው ማጠናቀቂያ መርሐ ግብር ላይ ለሥልጠናው መሳካት አስተዋጽኦ ላበረከቱ አጋር አካት እና አሠልጣኞች የዕውቅና እና የማበረታቻ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here