የስድስተኛ ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ዋና ዋና ነጥቦች፦

0
23
ባሕር ዳር: መስከረም 19/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት ተከናውኗል። የስደስተኛ ሳምንት የመጨረሻ ቀሪ ጨዋታ ዛሬ በኤቨርተንና ዌስትሃም መካከል ይካሄዳል።
ቅዳሜ እና እሑድ በተደረጉ ጨዋታዎች ደግሞ ያልተጠበቁ ውጤቶች የተመዘገቡበት፣ በዳኝነት ውሳኔም የተለያዩ ውዝግቦች የተነሱበት ነበር።
👉በሳምንቱ የሊቨርፑል በፓላስ 2ለ1 መሸነፍ ካልተጠበቁ ክስተቶች መካከል አንዱ ነው። ቀዮቹ በውድድር ዓመቱ ያስተናገዱት የመጀመሪያ ሽንፈታቸው ኾኖም ተመዝግቧል።
👉የቼልሲ ተጫዋቾች በተከታታይ ቀይ ካርድ መመልከት፦ ቼልሲ ባለፈው ሳምንት በማንቼስተር ዩናይትድ ተሸንፏል። የጨዋታው ውጤት ቀያሪ ሁነት ደግሞ ግብ ጠባቂው ሳንቼዝ ገና በጨዋታው የመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች በቀይ ካርድ መውጣት ነው።
ቼልሲ በዚህ ሳምንት ከብራይተን ጋር በነበረው ጨዋታ ተመሳሳይ ክስተት አስተናግዷል። ጨዋታውን 1ለ0 በጊዜ መምራት የጀመረው ቼልሲ በ53 ደቂቃ ቾሎባህን በቀይ አጧል። ይህን ተከትሎ ጨዋታውን 3ለ1 ተሸንፏል።
👉የማንቼስተር ዩናይትድ እና የአሠልጣኙ አሞሪም ስኬት አልባ ጉዞ፦ ወጣቱ አሠልጣኝ አሞሪም ኦልድትራፎርድ የሚኾናቸው አይመስልም። በስድስት የፕሪምየር ሊጉ ሦስቱን ተሸንፈዋል።
ያሸነፉት ሁለቱን ነው። ባለፈው ሳምንት ቼልሲ ላይ ባገኙት ሦስት ነጥብ መጠነኛ እፎይታ ላይ የነበሩት አሞሪም በብሬትፎርድ 3ለ1 በመሸነፍ የተዳፈነውን እሳት ጭረውታል።
👉የአርሰናል እልህ አስጨራሽ ትግል፦ አርሰናል በኒውካስትል በእጅጉ ተፈትኖ የማታ ማታ ሦስት ነጥብ ወስዷል። የአርቴታው ቡድን እስከ 84ተኛው ደቂቃ 1ለ0 ተመርቷል።
ተሸነፈ ሲባል በሚሪንሆ አማካኝነት አቻ ኾኖ በጨዋታው ጭማሪ ደቂቃ የማሸነፊያ ግብ አግኝቷል። ይህም ከሊቨርፑል ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት እንዲያጠብ አግዞታል
👉የአስቶን ቪላ ከሦስት ነጥብ ጋር መታረቅ፦ ባለፈው ዓመት አስደናቂ የውድድር ዓመት ያሳለፈው አስቶንቪላ ዘንድሮ ውጤት እንደሰማይ ርቆቷል። የኢምሬው ቡድን በአምስት የሊጉ ጨዋታዎች በሁለቱ ተሸንፎ፣ በሦስቱ አቻ በመውጣት ስደስተኛ ሳምንት ድረስ ጠብቋል። በመጨረሻም ፉልሃምን 3ለ1 በማሸነፍ ከሦስት ነጥብ ጋር ታርቋል።
👉በስድስተኛው ሳምንት በተደረጉ ዘጠኝ ጨዋታዎች 90 ደቂቃው ተጠናቅቆ በጭማሪ ደቂቃ ዘጠኝ ግቦች ተቆጥረዋል።
👉ሳምንቱ አወዛጋቢ የዳኝነት ውሳኔዎች የታዩበትና ቅሬታዎች የተሰሙበት ነው። ማይክል አርቴታ ቡድናቸው የፍጹም ቅጣት ምት ይገባው እንደነበር በማረጋገጥ የምስል ዳኝነትን ወቅሰዋል።
በተመሳሳይ ጨዋታ ኒውካስትል የፍጹም ቅጣት ምት ይገባኛል በሚል የዳኛውን ውሳኔ ተቃውሟል።
የማንቸስተር ዩናይትዱ ሩበን አሞሪምም በብሬንትፎርድ በተሸነፉበት ጨዋታ የዳኝነት ውሳኔዎች ሁሉ ከእኛ በተቃራኒ ነበሩ ብለው አማረዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here