ትራምፕ ከፊፋ ጋር እሰጥ አገባ የገቡበት የዓለም የወንዶች እግር ኳስ ጉዳይ

0
35
ባሕር ዳር: መስከረም 17/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የ2026 የዓለም የወንዶች እግር ኳስ ዋንጫን በጥምረት የሚያዘጋጁት አሜሪካ፣ ካናዳ እና ሜክስኮ ናቸው። በዚህ ውድድር 48 ሀገራት ተሳታፊም ይኾናሉ።
በአሜሪካ በኩል ጨዋታው በ11 ከተሞች ይካሄዳል። እነሱም አትላንታ፣ ቦስተን፣ ዳላስ፣ ሂዩስተን፣ ካንሳስ ሲቲ፣ ሎስ አንጀለስ፣ ማያሚ፣ ኒው ዮርክ፣ ፊላዴልፊያ፣ ሳን ፍራንሲስኮ እና ሲያትል ናቸው። በአሜሪካ፣ ካናዳ እና ሜክስኮ በተመረጡ ከተሞች 104 ጨዋታዎች ይደረጋሉ። ከነዚህ ውስጥ 78ቱ ጨዋታዎች ደግሞ በአሜሪካ ከተሞች የሚከናወኑ ይኾናል ተብሏል።
ጨዋታዎቹ የሚደረጉባቸውን ከተሞች መርምሮ የመምረጥ ኀላፊነት ያለበት ደግሞ ፊፋ ነው። ነገር ግን ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በፊፋ የተመረጡት ከተሞች የደህንነት ሥጋት አለባቸው በሚል ምክንያት ሥልጣናቸውን ተጠቅመው ወደ ሌላ ከተማ ሊቀይሩት እንደሚገደዱ ነው ከሰሞኑ ተናግረዋል። ትራምፕ በነጩ ቤተ መንግሥት ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት የዓለም ዋንጫ ጨዋታ የሚደረግበት ከተማ ሜዳ ደህንነቱ የተጠበቀ አይደለም ብዬ ካሰብኩ ወደ ሌላ ከተማ ለመቀየር ከማንም ጋር ሳልደራደር የመቀየር ኀላፊነቱ የእኔ ነው” ብለዋል።
ፊፋ በበኩሉ “አስተናጋጅ ከተሞችን እና የመጫዎቻ ሜዳ የመምረጥ ኀላፊነት ያለበት ትራምፕ ሳይኾኑ የፊፋ የሥራ ድርሻ ነው” በማለት በድረ ገጹ ምላሽ ሰጥቷል።ታዋቂ የእግር ኳስ ተንታኞች ታዲያ የ2026 የዓለም የእግር ኳስ ዋንጫ የሚተዳደረው (የሚመራው) በፊፋ ወይስ በአሜሪካ? ሲሉ መጠየቃቸውን ቢቢሲ እና ዴይሊ ሜይል ስፖርት በድረ ገጻቸው አስነብበዋል።
ዘጋቢ:- ሙሉጌታ ሙጨ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here