የኢትዮጵያ ወጣቶች ኦሎምፒክ በአዲስ አበባ ከተማ እንደሚካሄድ ተገለጸ።

0
12
አዲስ አበባ፡ መስከረም 14/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ሁለተኛው የኢትዮጵያ ወጣቶች ኦሎምፒክ ከጥቅምት 8/2018 ዓ.ም እስከ ጥቅምት 15/2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ በሰጠው መግለጫ አስታውቋል።
በዚህ ውድድር ዕድሜያቸው ከ14 ዓመት እስከ 17 ዓመት ያሉ ወጣቶች በ20 የስፖርት አይነቶች ተካፋይ ይኾናሉ። የኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን በኢንተርናሽናል ቦክስ አሶሴሽን ዕውቅና የሌለው በመኾኑ ቦክስ በዘንድሮው የታዳጊዎች ኦሎምፒክ አለመካተቱም ተመላክቷል።
በውድድሩ ሁሉም ክልሎች እና ከተማ አሥተዳደሮች ተሳታፊ እንደሚኾኑም የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ገልጿል። የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዝዳንት አሸብር ወልደጊዮርጊስ (ዶ.ር) ታዳጊዎች ላይ ትኩረት አድርጎ አለመሥራት የስፖርቱ ውድቀት አንዱ ምክንያት መኾኑን ተናግረዋል። መሰል ውድድሮችን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል።
የወጣት ውድድሮች በስፖርቱ ውስጥ የሚታየውን የዕድሜ ማጭበርበር ለመቆጣጠር አስፈላጊ መኾኑን እና ከፌዴሬሽኖች ጋር በቅንጅት በመሥራት ከውድድሩ በፊት አስፈላጊው የዕድሜ ምርመራ እንደሚደረግም ፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል። ከዚህ ውድድር የተመረጡ አትሌቶች በሴኔጋል ዳካር ለሚካሄደው የዓለም ወጣቶች ኦሎምፒክ እና በአንጎላ ለሚደረገው የአፍሪካ ወጣቶች ኦሎምፒክ ኢትዮጵያን ይወክላሉ ነው የተባለው።
የዓለም አቀፉ የወጣቶች ኦሎምፒክ ቀጣይ ዓመት በሴኔጋል ዳካር ሲካሄድ
የአፍሪካ ወጣቶች ኦሎምፒክ በታኅሣሥ 2018 ዓ.ም በአንጎላ ይደረጋል። ውድድሩ ለወጣቶች ዕድል ከመፍጠር ባለፈ በዓለም አቀፍ ደረጃ ኢትዮጵያን የሚወክሉ የነገ ተተኪ ስፖርተኞችን ማፍራት መኾኑንም የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ገልጿል። የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ወጣቶች ኦሎምፒክ ውድድር በ2014 ዓ.ም በሀዋሳ ከተማ መካሄዱ ይታወሳል።
ዘጋቢ:- ባዘዘው መኮንን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here