ቀጣዩ የባርሴሎና አሠልጣኝ ማን ይኾን?

0
306

ባሕር ዳር: ጥር 21/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የርገን ክሎፕ በዓመቱ መጨረሻ ሊቨርፑልን እንደሚለቁ መወሰናቸውን ተከትሎ የሊቨርፑል ቀጣዩ አሠልጣኝ ማን ይኾናል? የሚለው በብዙ አየተነሳ ነው።

በርካታ ውጤታማ አሠልጣኞችም የጀርመናዊውን ውጤታማነት እንዲያስቀጥሉ በሊቨርፑል ሊመረጡ ይችላሉ ተብሎ ስማቸው ተያይዟል።

ይህ የሊቨርፑል የአሠልጣኝ ምርጫ መቋጫ ሳያገኝ ለሥራ ፈላጊ አሠልጣኞች ሌላ መልካም ዜና ተሰምቷል። በውጤት ቀውስ የሚገኘው ባርሴሎና በውድድር ዓመቱ መጨረሻ ከዣቪ ጋር እንደሚለያይ አረጋግጧል። ይህን ተከትሎም ቀጣዩ የካታሎኑ ክለብ አሠልጣኝ እየተፈለገ ነው።

ቢቢሲን ጨምሮ የተለያዩ የመረጃ ምንጮች ቀጣይ የባርሴሎና አሠልጣኝ የመኾን እድል ያላቸውን አሠልጣኞች ጠቁመዋል።

የአርሰናሉ አሠልጣኝ ማይክል አርቴታ ቀዳሚው የባርሴሎና ምርጫ ነው እየተባለ ነው። አርቴታ በአርሰናል ያመጣው ለውጥ በባርሴሎና ተፈላጊ አድርጎታል።

በክለቡ የወጣት ቡድን ውስጥ ተጫውቶ ማለፉም ባርሴሎና አርቴታን ለማግኘት ይረደዋል ብሏል ቢቢሲ በዘገባው። ነገር ግን ስለጉዳዩ የተጠየቀው አርቴታ ከባርሴሎና ስሙ መያያዙ ትክክል አለመኾኑን ጠቅሷል። “አሁን በትክክለኛ ቦታና ሰዎች ውስጥ በመኾኔ ደስተኛ ነኝ” ሲል መልስ ሰጥቷል።

ጣሊያናዊ አንቶኒዮ ኮንቴ ለባርሴሎና አሠልጣኝነት የታጩ ሌላኛው አሠልጣኝ ናቸው። በጁቬንቱስ፣ ቼልሲና ኢንተርሚላን ውጤታማ የአሠልጣኝነት ጊዜ የነበራቸው ጣሊያናዊ አሠልጣኝ በባርሴሎና ቤት ላይቸገሩ እንደሚችል ተገምቷል።

የሊቨርፑል ቀዳሚ ምርጫ ይኾናሉ የተባሉት ሮቤርቶ ዲዘርቤም ከካታሎኑ ክለብ ጋር ስማቸው ተያይዟል። በብራይተን የሚያስመሰግን ሥራን የሠሩት ዲዘርቤ ስማቸው ከትላልቅ ክለቦች ጋር በተደጋጋሚ እየተነሳ ነው። በባርሴሎና መፈላጋቸውም የሚደንቅ አይደለም።

ለክለቡ አጨዋወት የተመቹ አሠልጣኝ መኾናቸውም የዣቪን መንበር ሊረከቡ ይችላሉ አስብሏቸዋል።

የፒኤስጂው አሠልጣኝ ሊዊስ ሄነሪኬ ከዚህ በፊት ባርሴሎናን ለሦስት ዓመታት መርተዋል። የተለያዩ ክብሮችንም አስመዝግበዋል። አሁንም በልኩ የማይገኘውን የድሮ ክለባቸውን ወደዝናው እንዲመልሱ ከታጩት ውስጥ ናቸው።

ጆዜ ሞሪንሆ ከሮማ ከተሰናበቱ በኃላ መዳረሻቸው አልታወቀም። ምናልባትም ልምድን ከውጤታማነት ጋር ያጣመሩትን ፖርቱጋላዊ ባርሴሎና ምርጫው ሊያደርጋቸው የሚችልበት እድል መኖሩን ዘገባዎች እያሰነበቡ ነው።

ነገር ግን በሪያል ማድሪድ ቤት አሠልጥነው ማለፋቸውና ከባርሴሎና ጋር በተጫወቱባቸው አጋጣሚዎች የፈጠሯቸው ውዝግቦች ሞሪንሆ ባርሴሎና የመድረሳቸውን ነገር አጠራጣሪ አድርጎታል።

በተጨማሪም የቀድሞ የክለቡ ተጫዋቾች ቲያጎ ሞታ፣ ራፋይል ማርኩየዝን ጨምሮ ሌሎች አሠልጣኞች የደከመውን ባርሴሎና ከዣቪ ተረክበው ወደዝናው እንዲመልሱት ታጭተዋል።

በአስማማው አማረ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here