ቀጣዩ የሥንብት ተረኛ ወይስ?

0
60
ባሕር ዳር: መስከረም 07/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ማንቸስተር ዩናይትድ በእንግሊዝ ብቻ ሳይኾን በዓለም እግር ኳስ ገናና ክለብ ነው። በዓለም ላይ በርካታ ደጋፊዎች አሉት።
ክለቡ በ90 የተለያዩ ሀገራት የተደራጁ ደጋፊዎች አሉት። እንደ ቢዝነስ ኦንላይን መረጃ 207 ሚሊዮን የማኅበራዊ ሚዲያ ተከታዮች ባለቤት ነው። ይህም ከሪያል ማድሪድ እና ባርሴሎና በመቀጠል ብዙ ተከታዮች ያሉት የዓለማችን ክለብ ያደርገዋል።
ክለቡ በ1990ዎቹ እና 2000ዎቹ በሰር አሌክስ ፈርጉሰን የነበረው ውጤታማነት ለትልቅነቱ ምክንያት ነው።
ነገር ግን ገናናው ክለብ አሁን የተቃራኒ ጉዞ ላይ ነው። ስኮትላንዳዊ አለቃ ሰር አሌክስ በዓለም እግር ኳስ ደረጃውን የሰቀሉት ክለብ አሁን ማንም የሚረታው ሆኗል። ሊገጥሙት ይፈሩ የነበሩት ክለቦች አሁን ከዩናይትድ ጋር መጫወትን እንደ እድለኝነት ይቆጥሩታል።
በእንግሊዝ አራተኛው ሊግ የሚጫወተው ግሪምስቢ በሊግ ካፕ ዩናይትድን ገጥሞ ባሸነፈበት ጨዋታ የግሪምስቢ ደጋፊዎች “እባካችሁ በየሳምንቱ ከእናንተ ጋር እንጫወት” በማለት መሳለቃቸው የዚህ ማሳያ ነው።
ክለቡ ውጤታማውን አሠልጣኝ ፈርጉሰንን በጡረታ ካጣ በኋላ ዳግም ወደ ኀያልነት ለመመለስ ያልፈነቀለው ድንጋይ የለም። በተለይ ውጤታማ አሠልጣኝ ለማግኘት ብዙዎችን ሞክሯል፤ የተፈተኑት ሁሉ ለኦልድ ትራፎርድ አለመጠኑም እንጂ።
የአሁኑ አለቃ ሩበን አሞሪምም ክለቡን ከማሻሻል ይልቅ ቁልቁል ያሮጡት ይዘዋል። አሠልጣኙ በዩናይትድ የ10 ወራት ቆይታቸው 46 ጨዋታዎች አድርገው ያሸነፉበት እና የተሸነፉበት የጨዋታ ቁጥር እኩል 17 ነው።
በፕሪምየር ሊጉ ብቻ 31 ጨዋታዎችን መርተው ስምንት ብቻ አሸንፈዋል። 16ቱን ሲሸነፉ በቀሪው ነጥብ ተጋርተዋል። በአማካይ በአንድ ጨዋታ አንድ ነጥብ ብቻ ያገኛሉ።
አሠልጣኙ ወደ ማንቸስተር ሲመጡ ብዙ ተስፋ ተጥሎባቸው ነበር። ነገር ግን ቁጥሮች የሚያሳዩት ክለቡ ከመሻሻል ይልቅ የቁልቁለት ሩጫ ላይ መኾኑን ነው። በዚህ የውድድር ዓመት በፕሪምየር ሊጉ በአራት ጨዋታ አራት ነጥብ ይዟል። ይሄም በክለቡ ታሪክ ከ1992/93 በኋላ ደካማው አጀማመር ነው።
በቅርቡ በኦልድ ትራፎርድ 20 ዓመታትን መቆየት እፈልጋለሁ ሲሉ የተደመጡት አሞሪም ሀሳባቸው የሚሳካ አይመስልም። ምክንያቱም በ31 ጨዋታ 31 ነጥብ እያስመዘገቡ የታላቁ ዩናይትድ ክለብ አሠልጣኝ ኾኖ መቀጠል አይችሉምና።
ክለቡን የሚመሩበት መንገድ ብዙ እያስተቻቸው ነው። የቀድሞው የዩናይትድ ተጫዋች ሮይ ኪን ዩናይትድን ጥራት እና ወኔ ያላቸው ተጫዋቾች የሌሉት ብሎ በስካይ ስፖርት ገልጾታል።
ከትናንቱ የደርቢ ሽንፈት በኋላም በማንቸስተር ደርቢ 3ለ0 ዩናይትድ ሲሸነፍ አንድም የዩናይትድ ተጫዋች ካርድ አልተመለከተም ይሄ ተጫዋቾች ለክለቡ ክብር የማይመጥኑ ወኔቢስ መኾናቸውን ያሳያል ብሏል ኪን።
ዋይኒ ሩኒም አሞሪም ዩናይትድን ከማሻሻል ይልቅ እያባባሱት ነው ብሏል። ለዝውውር 200 ሚሊዮን ፓውንድ ያወጡት አሠልጣኙ ክለባቸው በቅርቡ እንኳ የመሻሻል ምልክት እያሳየ አይደለም ሲል ጨምሯል።
የሚከተሉትን የ3,4,3 የጨዋታ ስልት ውጤታማ ባለመኾኑ ጥያቄ የበረታባቸው አሞሪም የጨዋታ ስልቴን አልቀይርም ብለው ሲሟገቱ በተደጋጋሚ ታይተዋል።
3,4,3 በተለይ የቡድኑ ወሳኝ ተጫዋች ቡርኖ ፈርናንዴስን ከጎል ርቆ እንዲጫወት እና ቡድኑም በተደጋጋሚ ለአደጋ እንዲጋለጥ አድርጎታል በሚል በተንታኞች እየተተቼ ነው።
የውጤት ማጣት፣ ከተጫዋቾች ጋር የሚፈጥሩት አለመግባባት እና ግትርነት ወጣቱ አሠልጣኝ ብዙ ተስፋ የጣለባቸው ክለብ በጊዜ እንዳይሸኛቸው ያሰጋል።
ሞሪንሆ፣ ቫንሃል፣ ሞይስ እና ቴንሃግን የመሳሰሉ አሠልጣኞች በሰፊው ለለመደው ዩናይትድ ደጋፊ ብቁ ኾነው አለተገኙምና የሽኝት ደብዳቤ ደርሷቸዋል።
አሞሪምስ? ሌላኛው የሥንብት ተረኛ ወይስ የቀጣዮቹ የ20 ዓመታት የዩናይትድ አለቃ?
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here