ባሕር ዳር: ነሐሴ 25/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ያለፉትን ረጅም ዓመታት በወጥነት በሀገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ መድረኮች በዳኝነት ያገለገለው ባምላክ ተሰማ ከዳኝነት ዓለም ራሱን ለማግለል መወሰኑን ለፊፋ በላከው መልዕክት ማሳወቁን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ይፋ አድርጓል፡፡
ኢንተርናሽናል ዳኛ ባምላክ ተሰማ በዓለም ዋንጫ፣ የአፍሪካ ዋንጫ፣ ቻን፣ ቻምፒየንስ ሊግ፣ ኮንፌሬዴሽን ዋንጫ፣ የዓለም ክለቦች ዋንጫ እና ኦሊምፒክን ጨምሮ በርካታ ሀገራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ታላላቅ ጨዋታዎችን በብቃት መርቷል፡፡ ኢትዮጵያን በሀገር አቀፍም ሆነ በዓለም አቀፍ መድረክ በማገልገሉ ኩራት እንደሚሰማው ገልጾ ፊፋ ለሰጠው ዕድል በማመስገን ከኢንተርናሽናል ዳኝነት ራሱን ማግለሉን አስታውቋል። ባምላክ ተሰማ በዳኝነት ላሳለፈው ህይወት እና አበርክቶ ያለውን አድናቆት እና ምስጋና የገለጸው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በዳኝነት ለሀገራችን ብሎም ለአፍሪካ ያበረከተው አስተዋፅኦ ሁሌም በኩራት የሚዘከር ነው ብሏል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!