“አሚኮ በስፖርት ዘርፍ የራሱ ቀለም ያለው ሚዲያ ነው” ጋዜጠኛ ሙሉቀን ሰጥዬ

0
102
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 15/2017 ዓ.ም (አሚኮ) አሚኮ 30ኛውን የምስረታ በዓል ምክንያት በማድረግ የሚዲያዎች እግር ኳስ ካፕ ውድድርን በባሕር ዳር ከተማ እያካሄደ ነው።
በመክፈቻ መርሐ ግብሩ መልዕክት ያስተላለፉ የአሚኮ ሥራ አሥፈጻሚ ጋዜጠኛ ሙሉቀን ሰጥዬ አሚኮ የውድድር ካፕ ሲያዘጋጅ የሚዲያ ተቋማትን አንድነት ለማጠናከር መኾኑን ነው የገለጹት። ሚዲያዎች በአንድ ዓላማ የምንሠራው ለሀገራችን አንድነት ነው ያሉት ጋዜጠኛ ሙሉቀን ሰጥዬ የውድድር መርሐ ግብሩ ኳስ ከመጫወት ባለፈ መስተጋብርን ለመፍጠር እና አብሮነትን ለማዳበር እንደኾነ ተናግረዋል። አሚኮ ባለፉት 30 ዓመታት በስፖርት ዘርፍ የሚሠራው ሥራ የራሱ ቀለም ያለው እና በብዙዎች ዘንድ የማይረሳ ትውስታን ጥሎ ያለፉ ሥራዎች መሥራቱን ነው ያመላከቱት።
አሚኮ ተመልካቾች እና አድማጮች በጉጉት የሚጠብቁት ብሎም በልዩ ሁኔታ የሚታወቅ የስፖርት ዘገባ ዝግጅት ያለው መኾኑንም ገልጸዋል።
“አሚኮ በስፖርት ዘርፍ የራሱ ቀለም ያለው ሚዲያ ነው” ብለዋል። በሬድዮ ቀጥታ ስርጭት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎችን፣ በባሕር ዳር የሚከናወኑ የብሔራዊ ቡድን እና የክለቦችን ጨዋታዎች በቀጥታ ስርጭት እስከ ማስተላለፍ የደረሰ ረጅም ልምድ ያለው ሚዲያ መኾኑንም ነው ዋና ሥራ አስፈጻሚው የተናገሩት። በአሁኑ ወቅትም በሬዲዮ፣ በቴሌቪዥን፣ በዲጅታል ሚዲያ እንዲሁም በጋዜጣ አማራጮች የስፖርት ትንታኔ ዘገባዎችን እየሠራ እንደሚገኝም አብራርተዋል።
በቀጣይም ባሕር ዳር የኢትዮጵያ የሚዲያ ካፕ እንዲኖር እንፈልጋለን ነው ያሉት። በውድድሩ ማጠናቀቂያም የሚዲያ ካፕ ፎረም እንደሚመሠረት ነው ያመላከቱት። የአዲስ ሚዲያ ኔትወርክ ጋዜጠኛ በረከት ወርቅነህ በበኩሉ ውድድሩ ከጨዋታ ባሻገር መቀራረብን ይፈጥራል ነው ያለው። ይህ መርሐ ግብር አሚኮ አዘጋጅቶ ስንጋበዝ ከፍተኛ ደስታ ተሰምቶኛል ብሏል። በቀጣይም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ጋዜጠኛ በረከት አስተያየቱን ሰጥቷል። በውድድሩ እየተሳተፈ የሚገኘው የኢቢሲ ጋዜጠኛ ነዋይ ይመር አሚኮ ያዘጋጀው ውድድር የተለያዩ የሚዲያ ጋዜጠኞችን ትስስር የሚፈጥር እና እርስ በእርስ ለመተዋወቅ ዕድል የሚፈጥር መኾኑንም ገልጿል። ውድድሩ ስፖርቱን ከመዘገብ ባለፈ ጋዜጠኞች በተግባር እንዲያልፉበት ያደርጋል ነው ያለው። ይህ ተግባር ተጠናክሮ በሌሎች ሚዲያዎችም መቀጠል እንደሚኖርበት አስተያየቱን ሰጥቷል።
ዘጋቢ፦ አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here