ባሕር ዳር: ነሐሴ 13/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአንዳንዶች ስኬት ከመቃብር በላይ ከፍ ብሎ ይኖራል። በዘመናቸው ብቻ ሳይኾን ያለ ዘመናቸውም ከፍ ብሎ ይታያል።
በኲር ጋዜጣ በየካቲት 18/2016 ዓ.ም ዕትሟ እንዳስነበበችው በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ ከጅማሬው ዘመን ጋር አብረው የሚነሱትን ይድነቃቸው ተሰማን አንስታለች። ይድነቃቸው ተሰማ ከታዳጊነት ዕድሜያቸው ጀምሮ እስካለፉበት ጊዜ ድረስ በተጫዋችነት፣ በአሠልጣኝነት፣ በዳኝነት እና በመሪነት ኢትዮጵያን እና አፍሪካን አገልግለዋል። የእርሳቸው ታሪክ ከመቃብራቸው በላይ ከፍ ብሎ ይኖራል። ‘ታላቁ የእግር ኳስ ሰው’ የሚለው ስያሜ ለእኝህ የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ኩራት ልካቸው አይመለስም። በእግር ኳስ ታሪክ ሁሌም ሊታወሱ እና ሊወደሱ የሚገባ ሰው ናቸው።
የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ኩራት ይድነቃቸው ተሰማ በእግር ኳስ ውስጥ በነበራቸው ሚና ዓለም አቀፍ የእግር ኳስ ውድድር አዘጋጅነት ወደ አፍሪካ እንዲመጣ ጥረት ያደርጉ ነበር። የአፍሪካ ሀገራት በዓለም ዋንጫ እንዲኖራቸው የሚፈቀደው የቡድኖች ቁጥር እንዲጨምርም ተግተዋል።
የካፍ ፕሬዝዳንት በመኾን ሕይወታቸው እስካለፈበት ጊዜ ድረስ ለአራት የሥልጣን ዘመናት አገልግለዋል።
በሥልጣን ዘመናቸው ትንባሆ እና የአልኮል ማስታወቂያዎች በአፍሪካ ስታዲየሞች እንዳይሰቀሉ አድርገዋል ይባልላቸዋል። በ1968 በአዲስ አበባ የጀመሩት የሥልጠና ፕሮጀክት በሁሉም የአፍሪካ ሀገራት እንዲስፋፋ በማድረግ በሺዎች የሚቆጠሩ አፍሪካውያን ዳኞች፣ አሠልጣኞች፣ እና ሌሎች ባለሙያዎች እንዲሠለጥኑ ማገዛቸው ይነገራል።
እኒህ በአፍሪካ የእግርኳስ ታሪን ገናና ስም ያላቸው ይድነቃቸው ተሰማ በነሐሴ 13/1979 ዓ.ም ነበር ያረፉት።ከሞታቸው በኋላ የቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብ የገነባውን ማሠልጠኛ በስማቸው በመጥራት ክብር ሰጥቷቸዋል። ሌሎች ተቋማትም በስማቸው ተሰይመዋል። ለሀገር ከሠሩት ሥራ አኳያ ግን አሁንም ከፍ ብለው ሊቀመጡ የሚገባቸው ሰው ናቸው።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን