አሚኮ በኢትዮጵያ ፕሪምዬር ሊግ አክሲዮን ማኅበር ላይ ቅሬታ አቀረበ።

0
88
አዲስ አበባ: ነሐሴ 12/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ፕሪምዬር ሊግ አክሲዮን ማኅበር በቀጣይ የውድድር ዓመት የሊጉን የቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት በሀገር ውስጥ ሚዲያዎች ለመሸፈን ያወጣው ግልጽ ያልኾነ ጨረታ ቅሬታ አስነስቷል።
የዘመናዊ ሚዲያ ቴክኖሎጂ ባለቤት እና ብቁ የሰው ኃይል ያለው አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽንም አክሲዮን ማኅበሩ ላይ ያለውን ቅሬታ በደብዳቤ አሳውቋል። ዲኤስ ቲቪ (DSTV) ከኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር ጋር የነበረው የአምስት ዓመታት ውል በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት 2017 ዓ.ም መጠናቀቁ ይታወቃል። ይህን ተከትሎም የሊጉን የቀጥታ ስርጭት ለሀገር ውስጥ ሚዲያዎች ለመስጠት አክሲዮን ማኅበሩ እንቅስቃሴ ላይ መኾኑ ቀደም ብሎም ሲገለጽ ቆይቷል።
የአክሲዮን ማኅበሩ ሥራ አሥኪያጅ ክፍሌ ሰይፈም በአንድ ወቅት ሁሉም አቅም ያላቸው የሀገር ውስጥ ሚዲያዎች በሚወጣው ጨረታ የመሳተፍ መብት እንዳላቸው ገልጸው ነበር። አክሲዮን ማኅበሩ ከአንድ ወር በፊት አውጥቶታል በተባለ ጨረታ አምስት የሚዲያ ተቋማት የጨረታ ሰነዱን መውሰዳቸው ተመላክቷል። ያለግልጽ ጨረታ ሚዲያዎች የተመረጡበት መንገድም ቅሬታን አስነስቷል። አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን (አሚኮ) በግልጽ ጨረታ ሁሉም ሚዲያዎች እንዲሳተፉ መደረግ ነበረበት አልያም ሚዲያዎች ያላቸውን አቅም ያማከለ መኾን ነበረበት ሲል ባቀረበው የቅሬታ ደብዳቤ አቋሙን አንፀባርቋል።
አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ለሀገር ውስጥ ስፖርት በተለይም ለእግር ኳሱ ዕድገት ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ የሚገኝ፣ ብቁ ባለሙያዎች ያሉት እና ዘመናዊ የሚዲያ ቴክኖሎጅን የታጠቀ መኾኑ ይታወቃል። በቅርቡም እጅግ ዘመናዊ ኦቢቫንን አስገብቷል። ይህ ዘመናዊ ኦቢቫን እግር ኳስን ጨምሮ የቀጥታ ስርጭት ሽፋን ለመስጠት አመች እና ተመራጭ ነው። አሚኮ የተንቀሳቃሽ ስቱዲዮ (ዲኤስኤንጅ) ባለቤትም ነው። አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዲኤስ ቲቪ ከመምጣቱ በፊትም የብሔራዊ ቡድን ጨዋታዎችን ጨምሮ ወደ ተለያዩ ከተሞች በመዟዟር የእግር ኳስ ጨዋታዎችን የቀጥታ ስርጭት ሽፋን በመስጠት ልምድ ያካበተ እና ብቁ ባለሙያዎች ያሉት የሚዲያ ተቋም ነው።
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር በቀጣይ የውድድር ዓመት የሊጉን የቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት በሀገር ውስጥ ሚዲያዎች ለመሸፈን ያወጣው ግልጽ ያልኾነ ጨረታ ይህን ትልቅ ተቋም አለማካተቱ ቅሬታ ፈጥኖብናል በማለትም ለሊጉ አሥተዳደር በደብዳቤ አሳውቋል። አክሲዮን ማኅበሩ የሚዲያ ተቋሙን ቅሬታ አይቶ ተገቢውን ምላሽ ይሰጣል የሚል ዕምነት እንዳለውም አሚኮ ገልጿል።
ዘጋቢ፡- ባዘዘው መኮንን
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here