ማንቸስተር ሲቲ ወደ ዎልቭስ ተጉዞ የሚያደርገው ጨዋታ ተጠባቂ ነው።

0
135
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 10/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የ2025/2026 የውድድር ዘመን የመጀመሪያ ሳምንት መርሐ ግብር ዛሬ ሲቀጥል ከሚካሄዱ ጨዋታዎች ማንቸስተር ሲቲ ወደ ወልቨስ ተጉዞ የሚያደርገው ጨዋታ ተጠባቂ ነው።
ማንቸስተር ሲቲ ለዘጠነኛ ተከታታይ ጊዜ የፕሪምየር ሊግ ውድድር ዘመንን ከሜዳው ውጭ ተጫውቷል። ከዚህ ቀደም ከስምንት ጨዋታዎች ሰባቱን አሸንፎ 19 ጎሎችን አስቆጥሮ ሁለት ጎሎችን ብቻ ነው ያስተናገደው። ከቅርብ 14 የውድድር ዘመናት 13ቱን የመጀመሪያውን የሊግ ጨዋታ አሸንፏል። ብቸኛው ሽንፈት በ2021/2022 የውድድር ዘመን በቶተንሃም ሆትስፐር 1 ለ 0 የተሸነፈበት ታሪኩ ነው። ማንቸስተር ሲቲ በአብዛኛው በዚህ ወቅት የሚያደርጋቸውን የፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች ባለመሸነፍ የሚታወቅ ጠንካራ ክለብ ነው። በቅርቡ ካደረጋቸው 31 ጨዋታዎች አንዱን ብቻ ነው የተሸነፈው።
ማንቸስተር ሲቲ አዲስ ያስፈረመው ሪያን አይት ኖሪ ከ2020 እስከ 2025 ድረስ በዎልቭስ 135 የሊግ ጨዋታዎችን አድርጓል። ሌላኛው አዲሱ የሲቲ ተጨዋች ሪያን ቼርኪ በፈረንሳይ ሊግ 1 ባለፈው የውድድር ዘመን 11 የግብ ኳስ በማቀበል ከፍተኛው ተጨዋች ነበር። ዎልቭስ ከ2013/14 እስከ 2020/21 ባሉት ስምንት ተከታታይ የውድድር ዘመናት በመጀመሪያው የሊግ ጨዋታው አልተሸነፈም። ይሁን እንጅ ከዚያ ወዲህ ባሉት አራት የውድድር ዘመናት የመጀመሪያውን ጨዋታ በሽንፈት ነው ያጠናቀቀው።
በ2024/25 የውድድር ዘመን በመጨረሻዎቹ አራት የፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች አንድም አላሸነፈም። የዛሬው ጨዋታ አስተናጋጅ ዎልቭስ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከማንቸስተር ሲቲ ጋር በፕሪምየር ሊግ ካደረጋቸው 10 ጨዋታዎች ውስጥ አንድ ብቻ ነው ያሸነፈው። ያሸነፈውም መስከረም 2023 በጋሪ ኦኔል አሠልጣኝነት ዘመን 2ለ1 በኾነ ውጤት ነበር።
የዎልቭስ አሠልጣኝ ቪቶር ፔሬራ በስድስት የተለያዩ ክለቦች በቆዩባቸው ዓመታት ከ10 የመክፈቻ የውድድር ዘመን ጨዋታዎች ስምንቱን አሸንፈዋል። ጉዳዩ ዛሬስ ይህንኑ ያለመሸነፍ ታሪክ ይደገሙታል የሚለው ይኾናል። ጨዋታው ምሽት 1:30 ሰዓት ላይ ይጀመራል። ሌሎች ጨዋታዎችም ዛሬ ሲቀጥሉ አስቶንቪላ ከኒውካስትል ቀን 8:30 ሰዓ፣ ብራይተን ከፉልሀም፣ ሰንደርላንድ ከዌስትሀም እና ቶተነሀም ከበርንለይ ቀን 11:00 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here