ጀግናው ሲታወስ

0
57
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 01/2017 ዓ.ም (አሚኮ)
“በጣም ደስ ብሎናል ምኞታችን ሞላ፤
አሸንፎ መጣ አበበ ቢቂላ” በማለት ገጣሚያን ስንኝ ቋጥረውለታል።
ነሐሴ 1/1924 ዓ.ም ጃቶ በተባለች አነስተኛ መንደር ተወለደ። የትውልድ ቀኑ ከ1932ቱ የሎስ አንጀለስ ኦሎምፒክ ጋር መገጣጠሙ ለትንሹ ልጅ ነገውን ያየለት አስመስሎታል። የእናቱ ስም ውድነሽ በነበሩ፣ የአባቱ ስም ቢቂላ ደምሴ ይባላሉ። አበበ በልጅነት ዘመኑ የገና ጨዋታን ያዘወትር እንደነበር ይነገርለታል።
በ20 ዓመት ዕድሜውም ወደ አዲስ አበባ በማቅናት የንጉሠ ነገሥቱን 5ኛ ሰልፈኛ ጦር ተቀላቅሏል። በጦሩ ውስጥ ሩጫን የጀመረው አበበ በጊዜው የሠራዊቱ ስፖርት አሠልጣኝ በነበሩት ኦኒ ኒስካነን የአትሌትነት አቅም እንዳለው ታይቶ ልዩ ሥልጠና ይሰጠው ጀመር። ሱሉልታ ድረስ በሚደረግ የ20 ኪሎ ሜትር ሩጫ እራሱን ማጠንከር የጀመረው አበበ ቢቂላ በንጉሣዊ ሠራዊቱ ስፖርታዊ ውድድር ዋሚ ቢራቱን ተከትሎ በመግባት የመጀመሪያ ማራቶኑን ማድረግ ችሏል።
ከዚያ በኋላ ተከታታይ ሁለት የማራቶን ውድድሮች በአንደኝነት ሲያጠናቅቅ በዓለም አቀፍ ደረጃ ባይመዘገብለትም በወቅቱ ያስመዘገበው 2:21:23 የማራቶን ሰዓት በኤሚል ዛቶፒክ ከተያዘው የዓለም ክብረወሰን ሰዓት የተሻለ ነበር። ከዚያም አበበ በ1960ው የሮም ኦሎምፒክ እንዲሳተፍ በአሠልጣኙ ኦኒ ኒስካነን አማካይነት ከሌላኛው ኢትዮጵያዊ አበበ ዋቅጂራ ጋር ቀረበ። አበበ ቢቂላ ከየውብዳር ወልደ ጊዮርጊስ ጋር ትዳር በመሠረተ ሥድስተኛ ወሩ በሮም አደባባይ የመጀመሪያ ዓለም አቀፍ ውድድሩን ለማድረግ ተሰለፈ።
42 ኪሎ ሜትሩ ከሚሸፍናቸው ጎዳናዎች መካከል የአክሱም ሐውልት ቆሞበት የነበረው ፒያዛ ደ ፖርቴ አንዱ ነው። ሯጮቹም ይህንን አደባባይ ለሁለት ጊዜ ሲዞሩ በአበበ አዕምሮ ውስጥ ተጨማሪ ሃሳብ መፈጠሩ እርግጥ ነበር። ይህ የቁጭት ሃሳብም ለአሸናፊነት ካስፈነጠሩት ምክንያቶች አንዱ እንደነበር ይታመናል።
በባዶ እግር ነገር ግን በፈጣን ሩጫ አበበ ቢቂላ ሮም ላይ ነገሠ። ከኦሎምፒክ ዶት ኮም የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው ማራቶኑን የገባበት ሰዓት ክብረወሰን ኾኖ ሲመዘገብ፤ በግሉ ከሰሀራ በታች ካሉ ሀገራት የመጀመሪያው የወርቅ አሸናፊ እና በአፍሪካ ደረጃ ክብረወሰን የሰበረ ስፖርተኛ አድርጎታል። ሀገር ቤት ሲመለስም የ10 አለቃነት ማዕረግ አግኝቷል።
ይህን የኦሎምፒክ ድሉን ዳግም ባስጠበቀበት የቶኪዮ ኦሎምፒክ ከ4 ዓመታት በኋላ ሌላ ታሪክ ሢሠራ ፑማ የጫማ ስፖንሠሩ ኾኗል። የሩጫ ልምድ እና ምቾትም አበበን ለሁለተኛ ጊዜ ክብረወሰን እንዲያሻሽል ያስቻለው ሲኾን ሩጫውን በ2:12:11 ሴኮንድ አጠናቅቆ ድሉን ድርብ አድርጓል።
በሁለተኛነት ያጠናቀቀው እንግሊዛዊው ባስሊ ሄትሊ ከአበበ በአራት ደቂቃዎች ዘግይቶ መግባቱም አበበ ቢቂላ የዘመኑ የማራቶን ጀግና ለመኾኑ ምስክር ኾኗል። ወደ ሀገሩ ሲገባም የምኒሊክ ኒሻን፤ ቮልስ ቫገን መኪና እና መኖሪያ ቤት ከግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ ተበርክቶለታል። ከነበረው ወታደራዊ አስር አለቃነት ማዕረግም ወደ መቶ አለቃነት ከፍ ብሏል።
ለወደፊትም ከሚነገሩለት ከእነዚህ ሁለት የኦሎምፒክ ድሎቹ ጋር አበበ በሩጫ ዘመኑ 16 የማራቶን ውድድሮችን አድርጓል። በሁለቱ ድሎች መካከልም በጀርመን በርሊን 10ሺህ ሜትር ሩጦ በ29 ደቂቃ የገባበት የሩጫ ታሪክ ካልተነገሩለት መካከል ነው። በጉልህ በሚታወቅበት ረጅም ርቀት ሩጫ ግን በቦስተን ማራቶን 5ኛ ከኾነበት እና የሜክሲኮ ኦሎምፒክን አቋርጦ ከወጣበት ውጭ 12 ውድድሮችን በቀዳሚነት ፈጽሟል።
ኢትዮጵያዊው የማራቶን ጀግና የሠራውን ያክል በሀገሩ የሚዘከርበት ልዩ መታወሻ ባይኖረውም ለምልክት የአበበ ቢቂላ ስታዲየምና በቀብሩ ቦታ የቆመለት የነሃስ ሐውልት ይታወሳሉ። ከቶኪዮ ድሉ መልስ በመኪና አደጋ እግሮቹን ለማዘዝ የተቸገረው አበበ ቢቂላ በአካል ጉዳተኞች ስፖርት በተለይም በጠረጴዛ ቴኒስ በለንደን እና በኦስሎ ሌላ ታሪክ መሥራቱ ይታወሳል።
ከጀግንነቱ ማሳያዎች መካከል የመኪና አደጋ አጋጥሞት ለንደን ለሕክምና በቆየባቸው ስምንት ወራት ንግሥት ኤልሳቤጥን ጨምሮ በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ሆስፒታል ድረስ ተመላልሰው ማጽናናታቸው የአበበን ትልቅነት መስካሪ ነበር። ጣልያን በዋና ከተማዋ ሮም ድልድይ እና የጎዳና ላይ መታሰቢያ በስሙ ስትሰይም፤ የስፖርት ጫማዎች አምራቹ ቪምራ በስሙ የተሰየሙ ጫማዎችን ለገበያ አብቅቷል። የኒውዮርክ የጎዳና ሩጫ አዘጋጆች የአበበ ቢቂላ ሽልማትን እስካሁን ለአሸናፊዎች የሚያበረክቱ ሲኾን ማሞ ወልዴ፣ ቲግላ ላሩፔ፣ ኃይሌ ገብረሥላሴ እና ሌሎች የዚህ ሽልማት ባለቤት ኾነዋል።
አበበ ቢቂላ በአትሌቲክስ ድሎቹ እስከ ሻምበልነት ማዕረግ በቅቷል። የተለያዩ ጸሐፍትም በተለያዩ ቋንቋዎች የሕይወት ታሪኩን እና ስኬቱን ከትበዋል። ከአራት ልጆቹ መካከል የኾኑት ፅጌ አበበ ታሪኩን ጽፈው ለአንባቢ ካበቁት መካከል ተጠቃሽ ናቸው። “አትሌቱ” በሚል ርዕስም ዘጋቢ ፊልም ተሰርቶለታል።
አበበ ቢቂላ በመኪና አደጋው ሰበብ የተፈጠረበት የጭንቅላት ሕመም በጥቅምት 14/1966 ዓ.ም ይህችን ዓለም በሞት እንዲሰናበት አድርጎታል። ህልፈቱ ብሔራዊ ሀዘን ኾኖ ሲታሰብ፤ የቀብር ሥነ ሥርዓቱም ንጉሠ ነገሥት ኃይለ ሥላሴን ጨምሮ ሺህዎች በታደሙበት በወታደራዊ አጀብ ተፈጽሟል። በ41 ዓመቱ ሩጫውን የፈፀመው የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ኩራት አበበ ቢቂላ ሥርዓተ ቀብሩ በቅዱስ ዮሴፍ ቤተክርስቲያን አርፎ ይገኛል።
በአማኑኤል ፀጋዬ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here