ብሔራዊ ቡድኑ በውጤት የታጀበ እና የአብሮነት ማጠናከሪያ እንዲኾን በትኩረት ይሠራል።

0
72

አዲስ አበባ: ሐምሌ 18/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ‎የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ደጋፊዎች ማኅበር የተመሠረተበትን 10ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።

ኢትዮጵያ የአፍሪካ እግር ኳስ ማኅበርን (የአሁኑ ካፍን) በመመሥረት ከግንባር ቀደምት ሀገራት መካከል ትጠቀሳለች። ብሔራዊ ቡድኑም በተለይ በአፍሪካ መድረክ የአፍሪካ ዋንጫን እስከማንሳት የደረሰ ታሪክ አለው።

በአሠልጣኝ ሰውነት ቢሻው የአሠልጠኝነት ዘመን ከ31 ዓመታት በኋላ ለአፍሪካ ዋንጫ ያለፈበት ክስተትም ለበርካቶች የሀሴት እና የአብሮነት ትዝታ ነው።

ብሔራዊ ቡድኑ በጥልቅ የደጋፊዎች ፍቅር የታጀበ እና ለውጤቱ መሻሻል የሚሠሩ አካላት ያሉበትም እንደኾነ ነው የተገለጸው።

የደጋፊዎችን አስተዋጽኦ በአሠራር ለመደገፍ ከ10 ዓመታት በፊት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ደጋፊዎች ማኅበር ተመሥርቷል።

ማኅበሩ የተመሠረተበትን 10ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግም ነው መግለጫ የሰጠው።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ደጋፊዎች ማኅበር የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ ሰለሞን ተሾመ የብሔራዊ ቡድኑ ደጋፊዎች ማኅበር በሀገር ፍቅር ስሜት የተመሠረተ እና ትስስርን የሚያጎላ፤ በውጤትም የታጀበ ብሔራዊ ቡድንን ለማየት የተመሠረተ ነው ብለዋል።

የደጋፊ ማኅበሩ ከመላው ሀገሪቱ የተውጣጡ አባላት አሉት ያሉት ኀላፊው በዚህም በጨዋታ ወቅት ብሔራዊ ቡድኑን በማበረታታት የላቀ ሚናን መወጣት ችሏል ነው ያሉት።

ማኅበሩ የበጎ ተግባራት ላይ በንቃት በመሳተፍ ማኅበራዊ ኅላፊነቱንም እየተወጣ መኾኑንም አንስተዋል።

በዚህ 10ኛ ዓመት የምስረታ በዓል አከባበር ጎን ለጎን ማኅበሩ አሠራሩን እና አደረጃጀቱን በመፈተሽ እና ዘመኑ የሚጠይቀውን በመከወን ለብሔራዊ ቡድኑ የእግር ኳሱ ዕድገት ይሠራል ብለዋል።

የዳጉ ኮሙኒኬሽን ዋና ሥራ አሥኪያጅ እና
የፕሮግራሙ አዘጋጅ ማናዬ እውነቱ የብሔራዊ ቡድኑ 10ኛ ዓመት ምሥረታን በማስመልከት የተለያዩ ሁነቶች ይዘጋጃሉ ነው ያሉት።

ከዝግጅቶቹ መካከልም፦

✍ የጽዳት ዘመቻ እና የጎዳና ላይ ትርኢት
✍የማስ ስፖርት
✍የዲፕሎማቲክ ስፖርት ፌስቲቫል
✍የዲያስፖራ ማኅበረሰብ የስፖርት ውድድር እና መሰል ተግባራት ለሦሰት ወራት ያህል ይከናወናሉ ብለዋል።

እነዚህን ሁነቶች ለመከዎን ተባባሪ ለኾኑ ተቋማትም ምሥጋና አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ደጋፊዎች ማኅበር ከቴምር ፕሮፐርቲስ ኀላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ጋር በጋራ ለመሥራት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል።

ዘጋቢ፦ አዲሱ ዳዊት

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here