ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 08/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ሊቨርፑል አሌክሳንደር ኢሳክን ከኒውካስትል ለማስፈረም እንቅስቃሴ ጀምሯል። የአንፊልዱ ክለብ ስዊድናዊውን አጥቂ ለረጅም ጊዜ ሲፈልገው ቆይቷል።
አኹን በአዲስ መልክ ተጫዋቹን ለማግኘት እንቅስቃሴ ጀምሯል። ኒውካስትል 120 ሚሊዮን ፖውንድ የተጫዋቹ ዋጋ መኾኑን አሳውቋል።
ሊቨርፑል የኢሳክ ፍላጎቱ ዳግም ያገረሸው ኒውካስትል ሁጎ ኢኪቴኪን ለማስፈረም ጫፍ መድረሱን ተከትሎ ነው።
👉በተመሳሳይ ሊቨርፑል በፊሊፕ ማቴታ ዝውውር ዙሪያ ከክርስቲያል ፓላስ ጋር ንግግር ጀምሯል። ተጫዋቹም ከሊቨርፑል ተወካዮች ጋር መገናኘቱን ፉትቦል መርካቶ አስነብቧል።
👉አርሰናል በክረምቱ ዝውውር የነቃ ተሳትፎ እያደረገ ነው። የተከላካይ እና አጥቂ ዝውውሮችን ለማጠናቀቅ የተቃረበው የለንደኑ ክለብ አሁንም ስሙ ከኢብሪቺ ኢዜ ጋር እየተነሳ ነው። ቶክ ስፖርት አርሰናል ለክለቡ ባለቤት ፓላስ ግልጽ ጥያቄ ለማቅረብ መዘጋጀቱን አስነብቧል።
👉ማንቸስተር ዩናይትድ ረጅም ጊዜ የወሰደበትን ብሪያን ሙቦሞን ዝውውር ለማጠናቀቅ ጫፍ ደርሷል። በተጫዋቹ ዝውውር ዙሪያ ዩናይትድ እና ብሬንትፎርድ ስምምነት አለመድረሳቸው ለዝውውሩ መዘግየት ምክንያት ነበር። በፉትቦል ትራንስፈር መረጃ መሠረት ሁለቱ ክለቦች አሁን ስምምነት ላይ ደርሰዋል።
👉ቤኔፊካ ጃኦ ፊልክስንን ከቼልሲ ለማስፈረም ንግግር ጀምሯል። ቼልሲ ተጫዋቹን በቋሚነት ለመሸጥ እንጅ በውሰት ለመስጠት ፍላጎት የለውም።
በአንጻሩ ቼልሲ ጋርናቾን ከማንቸስተር ዩናይትድ ማስፈረም እንደሚፈልግ እየተነገረ ነው።
👉ማንቸስተር ዩናይትድ ከሊዮኑ ኮረንቲን ቶሊሶን ጋር ስሙ ተያይዟል። የ30 ዓመቱ የመሀል ሜዳ ተጫዋች በአሠልጣኝ አሞሪም እይታ ውስጥ ይገኛል።
👉ሪያል ማድሪድ የአልቫሮ ካሪራስን ዝውውር አጠናቅቋል። የቀድሞው የዩናይት የታዳጊ ቡድን ተጫዋቹ ካሪራስ ከቤኔፊካ ነው ሪያል ማድሪድን የተቀላቀለው።
ዩናይትድም ቀድሞ በገባው ውል መሠረት ከተጫዋቹ ዝውውር የገንዘብ ተካፍይ ኾኗል።
👉የቀድሞው የሊቨርፑል አምበል ጆርዳን ሄንደርሰን ብሬንትፎርድን ተቀላቅሏል። ተጫዋቹ ከአያክስ ነው ለብሬንት ፎርድ የፈረመው።
በአስማማው አማረ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን