በኢትዮጵያ ፕሪምዬር ሊግ የፋሲል ከነማ እና ሀዋሳ ከተማ ጨዋታ ይጠበቃል።

0
100

ባሕር ዳር: ግንቦት 18/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የ31ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምዬር ሊግ ጨዋታ ዛሬ ሲካሄድ ፋሲል ከነማ ከሀዋሳ ከተማ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። በደረጃ ሰንጠረዡ ውስጥ በአንድ ነጥብ ልዩነት ተከታትለው የተቀመጡት ሁለቱ ቡድኖች ጥሩ ፉክክር ያደርጋሉ ተብሎ ነው የሚጠበቀው።
ፋሲል ከነማ በ36 ነጥብ 11ኛ ደረጃ ላይ ነው። ሀዋሳ ከተማ በ37 ነጥብ 10ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ፋሲል ከነማዎች ውጤት ከራቃቸው ስድስት ሳምንታት አልፏቸዋል። ከሦስት ተከታታይ ድሎች በኋላ በተደረጉ ስድስት ጨዋታዎች በሦስት ጨወታዎች ተሽንፈዋል። በሦስት ጨዋታ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። ቡድኑ ባለፉት ጨዋታዎች ግብ የማስቆጠር ምጣኔው ቀንሷል። ከዚህ ቀደም በሦስት ጨዋታዎች ስምንት ግቦችን ካስቆጠሩ በኋላ በመጨረሻዎቹ ስድስት ጨዋታዎች ሦስት ግቦችን ብቻ ነው ያስቆጠሩት። የዛሬው ተጋጣሚያቸው ፈታኝ ሊኾንባቸው እንደሚችል ነው የሚጠበቀው።

ሀዋሳዎች የቀድሞ ተጫዋቻቸውን አሠልጣኝ ሙሉጌታ ምሕረትን ከቀጠሩ በኋላ አስደናቂ መሻሻል በማሳየት ከወራጅ ቀጣና መውጣት ችለዋል። በሁለተኛው ዙር ከተደረጉ 11 ጨዋታዎች ውስጥ በመሪው መድን ከገጠማቸው ሽንፈት ውጭ በሌሎች ጨዋታዎች ሽንፈት አልገጠማቸውም። በተለይም በቅርቡ ባደረጓቸው ሦስት ተከታታይ ጨዋታዎች ድንቅ ብቃት አሳይተዋል፤ አራት ግቦችን በማስቆጠር አንድ ግብ ብቻ ተቆጥሮባቸዋል።

በሀዋሳ ከተማ በኩል ፍቃደሥላሴ ደሳለኝ በቅጣት ምክንያት ካለመሰለፉ ውጭ ሌሎች ተጫዋቾች ለጨዋታው ዝግጁ ናቸው። በፋሲል ከነማ በኩል ደግሞ አማኑኤል ገብረሚካኤል ከጉዳት አገግሞ ለጨዋታው ዝግጁ መኾኑ ተገልጿል። አቤል እንዳለ በጉዳት፣ ማርቲን ኪዛ በቅጣት ምክንያት አይሰለፉም።

ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም በ16 ጨዋታዎች ተገናኝተዋል። ፋሲል ከነማ 5 ጨዋታዎችን ሲያሸንፍ፣ ሀዋሳ ከተማ 4 ጊዜ አሸንፏል። ቀሪዎቹ 7 ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ተጠናቅቀዋል። ጨዋታው ምሽት 12:00 ሰዓት ይካሄዳል። ከፋሲል ከነማ እና ከሀዋሳ ከተማ ጨዋታ አስቀድሞ በስዑል ሽረ እና በመቀሌ 70 እንድርታ ቀን 9፡00 ይጫወታሉ።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here