ባሕር ዳር: ግንቦት 13/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኳሱ ንጉሥ ኬቨን ደህና ሁን። አንተ አትተካም። አንተ አትደገምም። አንተ አትረሳም እያሉ ዘመሩለት። ስታዲየም የሞላ ደጋፊ ሁሉ ስሙን እየጠራ አወደሰው፣ አሞገሰው። ለአብርክቶው ምሥጋና ሰጡት። ለተጋድሎው ዘመሩለት። ለብርታቱ አከበሩት።
ለዓመታት ከነገሠበት ስታዲየም ለመጨረሻ ጊዜ ተሰናብቷል። እጅ እየነሱ የተመኩበት ልዑል ተሰናብቷቸዋል። የመለያያ ጊዜያችን ደርሷል ብሎ ተለይቷቸዋል። ያን የመሠለ የማይደገም ልዑል ማሰናበት ስሜቱ ከባድ ነው። ነገር ግን አንድ ቀን መለያየት ግድ ይል ነበርና የመለያያ ጊዜያቸው ደረሰ።
ባለ ግራጫ ዓይኑ፣ ዝምተኛው ኮኮብ የማንቸስተር ሲቲ ደጋፊዎች በዘመናቸው አይተውት የማያውቁትን ክብር አሳይቷቸዋል። ከእንግሊዝ እስከ መላው አውሮፓ ድረስ ኀያል አድርጓቸዋል። በእግር ኳስ ከፍተኛውን ስኬት እንዲጨብጡ ፊታውራሪ ኾኗቸዋል። በጎረቤታቸው ለዓመታት ተወስዶ የነበረውን የበላይነት ነጥቆ የበላይነቱን ወደ ኢትሐድ መልሶላቸዋል። የኢትሐዱ ንጉሥ ኬቨን ዲብሮይን።
በተገፋባት የእንግሊዝ እግርኳስ ነገሠባት። በተገፋበት ፕሪምየር ሊግ የማይረሳ ታሪክ ጻፈበት። በፕሪምየር ሊጉ ታሪክም ከምርጥ ተጨዋቾች መካከል አንደኛው ኾነ። እርሱ በቸልሲ ቤት በቂ ቦታ የለህም ተብሎ ሲሰናበት እዚህ የብቃት ጫፍ ላይ ይደርሳል ብሎ የገመተ አልነበረም። እርሱ ግን በተገፋባት ሀገር ነግሦ ዓለምን አስደመመ።
በእንግሊዙ ክለብ ቸልሲ ቤት ቦታ የለህም ሲባል ወደ ጀርመኑ ክለብ ዎልፍስበርግ አቀና። ኬቨን በጀርመን አስደናቂ ጊዜን አሳለፈ። በዚህ ብቃቱ የታላላቅ ክለቦችን ቀልብ ሳበ። የማንቸስተር ሲቲ ሰዎችም ኬቨንን የግላቸው አደረጉት። ቤልጀማዊው አማካይ በ2015 ወደ ኢትሐድ አቀና። ኬቬን በእንግሊዝ ምድር ዳግም ብቃቱን የሚያሳይበት ዕድል አገኘ። ዕድሉን በሚገባ ተጠቀመበት። ማንነቱንም አሳየበት። በማንቸስተር ሲቲ ቤትም አስደናቂ ብቃትን አሳየ።
በፔፕ ጋርዲዮላ የሚመራው ማንቸስተር ሲቲ በታሪኩ የከፍታ ጫፍ ሲደርስ የኬቨን ዲብሮይን አስተዋጽኦው የላቀ ነበር። ኬቨን አትችሉም ተብለው ለተገፉ ሰዎች ምሳሌ ነው። ችሎ አሳይቷልና። ኬቨን የመገፋት እና የመነሳት ዘመን እንደሚመጣም ማሳያ ነው። ኬቨን በዝምታ ስኬትን የሚጨብጥ አርዓያም ነው።
ከአንደኛው ወደሌላኛው የሜዳ ጫፍ ኳሶችን በአስደናቂ ብቃት ያሻግራል። ለአጥቂዎች ለግብ የሚኾኑ ኳሶችን ያቀብላል። በወሳኝ ሰዓት የሚያስደንቁ ግቦችን ያስቆጥራል። እርሱ ካለ የማንቸስተር ሲቲ የጨዋታ ሚዛን ይጠበቃል። ቡድኑ ከተጋጣቢ ቡድን ልቆ ኳስ ይቆጣጠራል። ግብም ያስቆጥራል።
አሥርት ዓመታትን በኢትሐድ የነገሠው ኬቨን ከአሥርት ዓመታት በኋላ ከሲቲ ጋር እንደሚለያይ ማስታወቁ ይታወሳል። ይህ ንጉሥ ትናንት በኢትሐድ የመጨረሻ ጨዋታውን አድርጎ አሸኛኘት ተደርጎለታል። በስታዲየሙ ከአፍ እስከ ገደፍ የሞሉ ደጋፊዎች ከፍ አድርገው እየዘመሩ ሸኝተውታል።በስታዲየም የተገኙ ደጋፊዎች የኬቨንን ምስል በትልቁ ይዘው ንጉሥ ኬቨን ደህና ሁን ብለውታል። ብዙዎችም በእንባ ታጅበው ፍቅራቸውን ገልጸውለታል። እርሱ በማንቸስተር ሲቲ ታሪክ ውስጥ የደመቀውን ታሪክ ጽፏልና።
…
ቢቢሲ በዘገባው የማንቸስተር ሲቲ ደጋፊዎች ኬቨን ዲብሮይንን በእንባ ተሰናብተተውታል ብሏል። አሠልጣኙ ፔፕ ጋርዲዮላም አልቅሰውለታል። “ይህ ቀን የሀዘን ቀን ነው” ብለውለታል ፔፕ ጋርዲዮላ። እንባ በታጀበ ስሜት የተሸኘው ኬቨን ከጨዋታው በኋላ ባደረገው ንግግር ጥሩ ተጫዋች እንድኾን ብዙ ሰዎች አግዘውኛል ብሏል። በማንቸስተር ሲቲ ቤት ብዙ መልካም ነገሮችን እና በሕይወትም ታላላቅ ጓደኞችን እንዳገኘ ገልጿል።
ቢቢሲ በዘገባው ደብሮይና በአሥር ዓመታት ውስጥ ከዚህ በፊት በሲቲ ቤት ታይቶ የማይታወቅ ስኬት ያስመዘገበ ተጫዋች ነው ብሎታል። ይህን ታላቅ ታሪክ የጻፈን ተጨዋች ታዲያ የሲቲ ተጫዋቾች፣ ሠራተኞች እና ደጋፊዎች ክብር ሰጥተው ተሰናብተውታል። ነገር ግን በሲቲ ቤተሰብ ልብ ውስጥ እስከወዲያኛው ትኖራለህ ብለውታል።
ፔፕ ጋርዲዮላ በአሸኛኘቱ የማንቸስተር ሲቲ ሰዎች ምን ያህል ከኬቨን እና ከቤተሰቡ ጋር ግንኙነት እንዳላቸው፣ ምን ያህል ፍቅር እንዳላቸው ሁሉም አይቷል ብለዋል። ” ይህ ቀን የሚያሳዝን ቀን ነው፣ እሱ ይናፍቀኛል፣ ለዛ ምንም ጥርጥር የለውም” ነው ያሉት። ኬቨን የማንቸስተር ሲቲ ደጋፊ እንደኾነ እና ይህም ለዘለዓለም እንደሚኖር እርግጠኛ ነኝ።
ይህ የኾነው በሁሉም ሰዎች እና በእሱ መካከል ባለው ግንኙነት ምክንያት ነው ብለዋል። ባለ ግራጫ ዓይኑን ኮኮብ ዝምተኛ፣ ትሁት ይሉታል። የሲቲ ደጋፊዎች ኬቨን የመጨረሻውን ጨዋታ በሜዳው ሲያደርግ ኳስ በነካ ቁጥር የጉጉት ጩኸት ይጮሁ ነበር፣ ይህም ለመጨረሻ ጊዜ ግብ አግብቶ እንዲሰናበት ስለሚፈልጉ ነበር። ግን ይህ አልኾነም ኬቨን የስንብት ግብ አላስቆጠረም።
ግብ አለማስቆጠሩ የእርሱን ክብር እና ታላቅነት ግን አይቀንሰውም። ተጨማሪ ደስታ ይኾን ካልኾነ በስተቀር። “እንድትቆይ እንፈልጋለን፣ ኬቨን ዴብሩይን እንድትቆይ እንፈልጋለን ” ከደጋፊዎች የዘለቀው ዝማሬ ነበር። ነገር ግን ወደ ኋላ አይመለስም። እርሱ ተሰናብቷልና። ኬቨን ለተጨማሪ ዓመታት በሲቲ ቤት እንዲቆይ ውል ሳይቀርበለት በመቅረቱ ብዙዎችን አስገርሟል። ስለ ምን ቢሉ እርሱ አኹንም በታላቅነት መጫወት ይችላልና።
የቀድሞው የማንቸስተር ሲቲ ተጨዋቾች ምን ያህል ትሑት እንደኾነ እና ምን ያህል ታላቅ ተጫዋች እንደኾነ አይተነዋል ብለውታል። ኬቨን ማንቸስተር ሲቲ ለእርሱ ምን ማለት እንደኾነ ሲጠየቅ ቤቴ እና ቤተሰቤ ብሏል። የቀድሞ የሊቨርፑል አማካኝ ጃሚ ሬድናፕ በስካይ ስፖርት ላይ እንዲህ ብሏል “በዓለም እግር ኳስ ቀጣዩ ዲብሮይን ማን ነው? አይኖርም። እርሱ የተለየ ነው። ስለዚህ ሌላ ኬቨንን ለመፈለግ እንኳን አትቸኩሉ። እርሱ የእግር ኳስ ሊቅ እንደኾነ ምንም ጥርጥር የለውም” ብሏል።
አልጀዚራ በዘገባው የማንቸስተር ሲቲው አሠልጣኝ ፔፕ ጋርዲዮላ በኢትሐድ ስታዲየም የነበረውን አስደናቂ የአሥርት ዓመታት ቆይታ መጋረጃ ከዘጋው አምበሉ ኬቨን ጋር በእንባ ተሰነባብተዋል ብሏል። ኬቨን በኢትሐድ ስታዲየም ሐውልት እንደሚቆምለትም ተገልጿል። የቀድሞ የቡድን አጋሩ ሲርጂዮ አጉየሮ ደግሞ “ከአንተ ጋር መጫወት ትልቅ ክብር ነበር፣ መልካሙን ሁሉ እመኝልሃለሁ፣ በእርግጥ አንተ በማንቸስተር ሲቲ ውስጥ ጀግና ነህ” ብሎታል።
የኢትሐዱ ንጉሥ ተሰናብቷል። ፊቱን ለሌላ ፈተና አዙሯል። በማን መለያ ይታይ ይኾን ? የሚለው ደግሞ በጉጉት ይጠበቃል።
በታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን