በሀንሲ ፍሊክ የተሳለው ባርሴሎና!

0
106

ባሕር ዳር: ግንቦት 08/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በዓለም እግር ኳስ ስማቸው የገነነ ተጫዋቾችን በማፍራት ይታወቃል። በስፔን እና አውሮፓ ግዙፍ ከሚባሉ ክለቦች መካከልም አንዱ ነው ባርሴሎና። ክለቡ በላሊጋው 28 ጊዜ ዋንጫ አንስቷል፤ በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግም አምስት ጊዜ ድል አድርጓል። ሌሎች ዋንጫዎችን እና ክብሮችን መሠብሰብ የቻለ በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚሊዮን ደጋፊዎችን ያፈራ ክለብ ነው።

ክለቡ ባለፉት ሁለት ዓመታት በቀድሞው የክለቡ ድንቅ ተጫዋች ዣቪ አሠልጣኝነት ሲመራ ነበር። ዣቪ በመጀመሪያ ዓመቱ ክለቡ የላሊጋ ዋንጫ እንዲያነሳ አድርጓል። ነገር ግን ክለቡ የሚታወቅበትን የአጨዋወት ስልት በማስቀጠል እና ወጥነት የጎደለው እንቅስቃሴ በተጫዋችነት በነገሰበት ኑ ካፕ በአሠልጣኝነት መድገም ሳይችል እንዲሰናበት ምክንያት ኾኗል።

ባርሴሎና ዣቪን አሰናብቶ ጀርመናዊ ሀንሲ ፍሊክን በመቅጠር ነው የዘንድሮውን የውድድር ዘመን የጀመረው። ክለቡ በገንዘብ ችግር ምክንያት ተጫዋቾችን ማስፈረም ባይችልም በላማሲያ አካዳሚ ውጤት በኾኑ ተጫዋቾች አማካኝነት ዓመቱን በድምቀት አሳልፏል። ሀንሲ ፍሊክም ክለቡ ላይ የፈጠሩት አብዮት በብዙ እያሥመሠገናቸው ነው። የላሊጋውን ዋንጫ ጨምሮ የካታሎኑ ክለብ በውድድር ዓመቱ ሦስት ዋንጫዎችን ስሟል። በአውሮፖ ሻምፒዮንስ ሊግ በአሳማኝ እንቅስቃሴ ግማሽ ፍጻሜ ድረስ ተጉዟል።

ከባለፉት ዓመታት አጅግ የተሻሻለውን ባርሴሎና ፍሊክ አሳይተዋል። በታዳጊዎች የተዋቀረው የሀንሲ ፍሊኩ ቡድን በማጥቃቱ እጅግ አስፈሪ ኾኖ ቀርቧል። የሉዋንዶስኪ፣ ያማል እና ራፊኛህ ጥምረት ታላላቅ በሚባሉ ቡድኖች ላይ ሳይቀር ምረት የለሽ ኾኖ ታይቷል። ባየር ሙኒክ እና ሪያል ማድሪድ ደግሞ ለዚህ ምሳሌ ናቸው። ባየር ሙኒክ በሻምፒዮንስ ሊጉ፣ ሪያል ማድሪድ ደግሞ በላሊጋው በደርሶ መልስ እና በኮፓ ዴላሬይ እና ሱፐር ካፕ ዋንጫ በካታሎኑ ክለብ የግብ ናዳን የቀመሱ ክለቦች ናቸው።

ያሆ ስፖርት የዘንድሮው የባርሴሎና ቡድን በላሊጋው በአማካኝ ዕድሜ ትንሹ ቡድን መኾኑን ይገልጻል። የክለቡ አመካኝ ዕድሜ ደግሞ 24 መኾኑን ያስረዳል። የላማሲያ ፍሬዎቹ ፔድሪ፣ ያማል እና ባልዴ ቀደም ብለው የክለቡ ሁነኛ ተጫዋች ኾነዋል። ዘንድሮ ደግሞ ሎፔዝ እና ኩባርሲን የመሳሰሉ ተጫዋቾች ከዕድሜያቸው በላይ ክለቡን እያገለገሉ ነው።

ባርሴሎና አኹን ላለበት የተሳካ መንገድ ከአካዳሚው ላማሲያ በተጨማሪ ለጀርመናዊ አሠልጣኝ ሀንሲ ፍሊክ ምሥጋና እየጎረፈላቸው ነው። አሠልጣኙ በመጀመሪያ ዓመት ቆይታቸው ሦስት ዋንጫ አንስተዋል፤ በባርሴሎና የምንጊዜም ተቀናቃኝ ሪያል ማድሪድ ላይ የወሰዱት የእርስ በእርስ የበላይነትም ለባርሴሎና ደጋፊዎች ቅቤ እንደመጠጣት ነው።

ባርሴሎና ዘንድሮ በላሊጋው ሁለት ጨዋታዎች እየቀሩ 97 ግቦችን አስቆጥሯል። በአማካኝ በጨዋታ 2 ነጥብ 6 ግብ አስቆጥሯል ማለትም ነው። ይሄ በላሊጋው ቀዳሚ ክለብ ሲያደርገው ከአምስቱ የአውሮፓ ታላላቅ ሊጎች ደግሞ ከባየርሙኒክ እና ፒኤስጅ በመቀጠል ሦስተኛ ምርጥ አጥቂ ቡድን ያደርገዋል።

አንጋፋው ሮበርት ሉዋንዶስኪ 25 ግቦችን በላሊጋው ሲያስቆጥር፣ ራፊኛህ 18 ግቦችን አስቆጥሯል። ታዳጊው ያሚን ያማል 13 ለግብ የኾኑ ኳሶችን በማመቻቸት ቀዳሚው የላሊጋ ተጫዋች ነው። ያስቆጠራቸው ሰባት ግቦችም ለባርሴሎና የላሊጋ ድል ትልቅ ሚና ነበራቸው። ማራኪው የሀንሲ ፍሊክ የጨዋታ አቀራረብ በመከላከልም ተመስጋኝ ነው። እስከ ሊጉ 36ኛ ሳምንት ድረስ የተቆጠረበት 36 ግብ ነው። ከአትሌቲክ ክለብ እና አትሌቲኮ ማድሪድ በመቀጠል መረቡን ባለማስደፈር የተሻለ ቡድንም ነው።

ቡድኑ በዓመቱ በአማካይ በ68 ነጥብ 7 በመቶ ኳስን ተቆጣጥሮም ተጫውቷል። ከምንም በላይ ፔድሪ፣ ያማል፣ ኩባርሲ እና የመሳሰሉ የላማሲያ ምሩቆችን ወደ ታላቅነት ያመጡበት መንገድም ጀርመናዊውን አሠልጣኝ እያስወደሳቸው ነው። ይሄ ለሦስት ዋንጫ ያበቁት ቡድናቸው አማካኝ ዕድሜ ገና 24 መኾኑ ሲታሰብም በሀንሲ አሠልጣኝነት በካታሎኒያ ብዙ ሊያሳይ እንደሚችል መገመት ቀላል ነው።

በጋርዲዮላ ዘመን የተቃኘው የመሲ ዘመን የባርሴሎና ልዕልና በቀጣይ በሀንሲ ፍሊክ መሪነት እና በያማል ትልቅነት መመለሱ አይቀሬም ይመስላል።

በአስማማው አማረ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here