የዣቪ አሎንሶ ስንብት!

0
127

ባሕር ዳር: ግንቦት 04/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ስፔናዊው አሠልጣኝ ዣቪ አሎንሶ ባለፉት ሁለት ዓመታት በጀርመን ለተአምር የቀረበ ሥራ ሠርቶ ብዙዎችን አስደምሟል። አሠልጣኙ ላለመውረድ የሚንገዳገደውን ባየርሊቨርኩሰንን ከሁለት ዓመት በፊት ተረክቧል።

ከዚያ በፊት የአሠልጣኝነት ልምድ የሌለው አሎንሶ ቡድኑን በወራት ውስጥ ከመውረድ አተረፈው።

ባለፈው ዓመት ደግሞ ህልም የመሰለውን እውነት አሳካ። ባየርሊቨርኩሰን ከግዙፉ ባየርሙኒክ በላይ ኾኖ የቦንደስ ሊጋን ዋንጫ አነሳ። ይህ ክስተት በጀርመን ብቻ ሳይኾን በዓለም እግር ኳስ አፍቃሪያን ዘንድ የአሎንሶን ዋጋ ከፍ አደረገው።

ሊቨርፑል የርገን ክሎፕን ለመተካት የመጀመሪያ ምርጫው አሎንሶን ማግኘት ነበር። ቀዮቹ ብዙ ሙከራ ቢያደርጉም ስፔናዊው ለጀርመኑ ክለብ መታመኑን መርጧል።

በሊቨርኩሰን ደጋፊዎች በአጭር ጊዜ የተወደደው አሎንሶ አሁን የስኬት ምልክት ከኾነበት ቤት ለመውጣት በሩ ላይ ይገኛል። የአሎንሶ ከፍታ እድገቱ ቀጥሏል። አሁን የሪያል ማድሪድ አሠልጣኝ ለመኾን ተቃርቧል።

ስፔናዊው በስፔኑ ግዙፍ ክለብ ሊፈተን የሦስት ዓመታት ውል ለመፈረም መስማማቱን ፉትቦል ለንደንን ጨምሮ በርካታ የእግር ኳስ ምንጮች አስነብበዋል።

ሊቨርኩሰን ትናንት ከዶርትሙንድ ጋር ካደረገው ጨዋታ በኋላ አሎንሶ በክለቡ ደጋፊዎች ደማቅ ሽኝት ተደርጎለታል። ቡድኑ በሜዳው ሽንፈት ቢገጥመውም ደጋፊዎቹ በተለየ ስሜት አሎንሶን አክብረውታል።

ሊቨርኩሰን በሊጉ በ68 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ሲኾን የትናንቱ ጨዋታ የዚህ ውድድር ዓመት በሜዳው ያደረገው የመጨረሻ ጨዋታው ነው።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here