ፒኤስጂ ወይስ አርሰናል?

0
211

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 29/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ኢንተር ሚላንን ለፍጻሜ ያደረሰው የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታ ዛሬ ሌላኛውን የፍጻሜ ተፋላሚ ይለያል።

ከኢንተር ሚላን ጋር የፍጻሜ ተፋላሚ የሚኾነው የፈረንሳዩ ፒኤስጂ ወይስ የእንግሊዙ አርሰናል የሚለው በጉጉት ይጠበቃል። በመጀመሪያው የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ ወደ እንግሊዝ ተጉዞ ድል አድርጎ የተመለሰው ፒኤስጂ ዛሬ በሜዳውና እና በደጋፊው ፊት የመልሱን ጨዋታ ያደርጋል።

በሜዳው እና በደጋፊው ፊት የተሸነፈው አርሰናል ከሜዳው ውጭ የሚያደርገው ጨዋታ እንደሚከብደው ይጠበቃል።

ከስድስት የእርስ በእርስ ግንኙነቶች በኋላ አርሰናል ላይ ድል የቀናው ፒኤስጂ በዛሬው ጨዋታ የተሻለ እድል ይዞ ወደሜዳ ይገባል። አርሰናል ከፈረንሳይ ክለቦች ጋር ከሜዳ ውጭ ያደረጋቸው ጨዋታዎች በጥሩ ውጤት ቢያጠናቅቅም የዛሬው ጨዋታ ግን ከባድ ፈተና እንደሚኾን ይጠበቃል።

በሻምፒዮንስ ሊግ ታሪክ የመጀመሪያውን የሜዳቸውን ጨዋታ ተሸንፈው ለፍፃሜው ጨዋታ የደረሱ ሁለት ቡድኖች ብቻ ናቸው። በ1995/96 አያክስ ፓናተናይኮስን አሸንፎ ለፍጻሜ ሲደርስ፣ በ2018/19 ደግሞ ቶተንሃም አያክስን አሸንፎ ለፍጻሜ ደርሷል።

ፓሪስ ሴንት ዠርመን እና አርሰናል ለሁለተኛ ጊዜ የሻምፒዮንስ ሊግ ፍፃሜ ለመድረስ ነው የሚፋለሙት። ፓሪስ ሴንት ዠርመን በ2019/20 እና አርሰናል በ2005/06 ከፍጻሜ ደርሰው እንደነበር ቢቢሲ በዘገባው አመላክቷል።

አርሰናል የመጀመሪያውን የሜዳውን ጨዋታ ከተሸነፈ በኋላ ወደ ቀጣዩ ዙር ያለፈበት ጊዜ አለመኖሩም ተገልጿል።

ፒኤስጂ በዚህ የውድድር ዓመት በሻምፒዮንስ ሊጉ በሜዳው ሁለት ጊዜ ተሸንፏል። ሊቨርፑል እና አትሌቲኮ ማድሪድ ደግሞ የአሸነፉት ቡድኖች ናቸው።

አርሰናል በቅርብ ጊዜ ባደረጋቸው አራት የሻምፒዮንስ ሊግ የሜዳ ውጭ ጨዋታዎች አሸንፏል።

የዓለም እግር ኳስ አፍቃሪያን የሚጠብቁት የፒኤስጂ እና የአርሰናል ጨዋታ 4:00 ይካሄዳል። የፍጻሜውን ትኬት ማን ይቆርጥ ይኾን የሚለው በጉጉት ይጠበቃል።

ዘጋቢ:- ምሥጋናው ብርሃኔ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here