በአንፊልድ ከግምቶች በላይ!

0
124

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 20/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ሊቨርፑል ባለፉት ዓመታት በጀርመናዊ አሠልጣኝ የርገን ክሎፕ እየተመራ የተሻለ ጊዜን አሳልፏል። የፕሪምየር ሊግ እና ሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን ለቀዮቹ ያስገኙት ክሎፕ በአንፊልድ ተወዳጅ ነበሩ።

ነገር ግን ባለፈው ዓመት የውድድር መጨረሻ ላይ ‘አንቱ’ ከተሰኙበት ክለብ ጋር ተለያይተዋል። ክለቡ እሳቸውን ለመተካት ዣቪ አሎንሶን ለመቅጠር ብዙ ቢወጣ ቢወርድም አልተሳካለትም።

ይህን ተከትሎ ብዙም በስኬታቸው የማይታወቁትን አርኔ ስሎትን ቀጥሯል። በትልቅ ሊግ የማሠልጠን ልምድ የሌላቸው ስሎት በታላቁ የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ይሳካላቸው ይኾን የሚለው ጥያቄ የብዙዎች ነበር።

በስኬታማው ክለብ ስኬታማውን አሠልጣኝ እንደሚተኩ ሲታሰብ ደግሞ የክለቡን ውሳኔ የተሳሳተ ለማለት የቀደሙ ብዙዎች ነበሩ።

አኹን ሆላንዳዊ አሠልጣኝ ተችዎችን አፍ አስይዘዋል። በዓመቱ መጀመሪያ ለዋንጫ አሸናፊነት ከተገመቱት የጋርዲዮላው ማንቸስተር ሲቲ እና የአርቲታው አርሰናል በላይ ሊቨርፑልን አስቀምጠዋልና።

በፕሪምየር ሊጉ ቀሪ አራት ጨዋታዎች እየቀሩ የዋንጫ ባለቤት መኾናቸውም ብዙ አድናቆት አስግኝቶላቸዋል።

እንዲህ በጊዜ ክለቡ ውጤታማ ያደረጉት ስሎት በሊቨርፑል የአንፊልድን ሙቀት እንደሚያስቀጥሉ እምነት አግኝቷል።

ከውጤቱ በተጨማሪ ግን ክለቡ በአዲሱ አሠልጣኝ ኳስ የሚጫወትበት መንገድ ለታማኞቹ የአንፊልድ ደጋፊዎች በክሎፕ ትዝታ እንዳይቆዝሙ አድርጓል።

ቢቢሲ በስፖርት ገጹ የስሎቱ ሊቨርፑል ከክሎፑ ቡድን ጋር በአጨዋወት በብዙ እንደሚመሳሰል ጽፏል። በመጠኑም ቢኾን ግን የስሎቱ ሊቨርፑል የተሻለ ነገር አለው።

በየጨዋታው በተጋጣሚዎቹ ላይ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ መውሰድ፣ ቀጥተኛ የማጥቃት ስልትን መተግበር እና የኳስ ቅብብል ስኬት ክለቡ ካለፉት ዓመታት ተሽሎ ከታየባቸው ውስጥ መጥቀስ ይቻላል።

አሁን እንደተፈራው አንፊልድ በክሎፕ ሀንጎበር አልተቸገረም። ይልቁንም አዲሱ አሠልጣኝ በስማቸው እየተዘመረላቸው ነው። በአንፊልድ ነገሮች የሰመሩ ኾነዋል። ቀዮቹም የፕሪምየር ሊግ ዋንጫን በታሪካቸው ለ20ኛ ጊዜ ከፍ አድርገዋል።

ይሄም ከታሪካዊ ተቀናቃኛቸው ማንቸስተር ዩናይትድ እንዲስተካከሉ አድርጓቸዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here