ኤልክላሲኮ-ከእግር ኳስም በላይ!

0
125

ባሕር ዳር:ሚያዝያ 17/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ቅዳሜ ሚያዝያ 18/ 2017 ምሽት አምስት ሰዓት ሲኾን የእግር ኳሱን ዓለም በአውሎ ንፋስ የሚወስደው “ኤል ክላሲኮ” በመባል የሚታወቀው የባርሴሎና እና ሪያል ማድሪድ ጨዋታ ፍጥጫ በቴሌቪዥን መስኮታችን ብቅ ይላል። ይህ ጨዋታ ከማንኛውም የእግር ኳስ ግጥሚያ በላይ ነው። ይህ ፍጥጫ የስፖርታዊ ፉክክር ብቻ ሳይኾን የሁለት ታላላቅ ከተሞች፣ የሁለት የተለያዩ ባሕሎች እና የሁለት ተቃራኒ የእግር ኳስ ፍልስፍናዎች ግጭት ነው።

የባርሴሎና እና ሪያል ማድሪድ ፍጥጫ ከእግር ኳስ ሜዳ በላይ የዘለቀ ነው። ሁለቱ ክለቦች የስፔንን ሁለቱን ትልልቅ ከተሞች ይወክላሉ። ባርሴሎና የካታላን ብሔርተኝነት ምልክት ሲኾን ሪያል ማድሪድ ደግሞ የስፔን ማዕከላዊ መንግሥትን ይወክላል። ይህ የፖለቲካ እና የባሕል ልዩነት በሜዳው ላይ በሚደረገው ፉክክር ላይ ተጨማሪ ቅመም ይጨምራል።

በታሪካቸው ሁለቱም ክለቦች እንደ ሊዮኔል ሜሲ፣ ክርስቲያኖ ሮናልዶ፣ ጆሃን ክራይፍ፣ አልፍሬዶ ዲ ስቴፋኖ እና ዚነዲን ዚዳን ያሉ ምርጥ ተጫዋቾችን አፍርተዋል። የእነዚህ ተጫዋቾች ክለባቸውን ለማሸነፍ ያደረጉት ጥረት የክለቦቹን ጨዋታዎች ክብር እና ታላቅነት ጨምሯል።ኤል ክላሲኮ የእግር ኳስ አፍቃሪዎችን ቀልብ የሚስብ እና ወደ ስታዲየም እና ቴሌቪዥን ስክሪኖች በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ተመልካቾችን የሚስብ ክስተት ነው።

የውጤቱ እርግጠኛ አለመኾኑን ብሎም አስደናቂ ግቦች እና ከፍተኛ ፉክክር እያንዳንዱን ጨዋታ የማይረሳ ያደርገዋል። የባርሴሎና እና ሪያል ማድሪድ ፍጥጫ በዘመናዊ እግር ኳስ ውስጥ በጣም አስፈላጊ ከኾኑት ክስተቶች አንዱ ነው። የእነዚህ ሁለት ታላላቅ ክለቦች ታሪክ፣ የአሁኑ የውድድር ዘመን እንቅስቃሴ እና የቀድሞ ግጥሚያዎች ይህንን ፉክክር ልዩ እና የማይረሳ ያደርጉታል።

ይህ የተቀራረበ ዘመን ያልሻረው ፍጥጫ አሁንም ድምቀቱ እንደቀጠለ ነው። ባርሴሎና እና ሪያል ማድሪድ በሁሉም ውድድሮች 91 ጊዜ ተገናኝተዋል። ከእነዚህም ባርሴሎና 41 ጊዜ ሲያሸንፍ ሪያል ማድሪድ 30 ጊዜ አሸፏል። 20 ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል።

የአሁኑን የዋንጫ በፍልሚያ ማን ያሸንፋል በርግጥ መገመት አይቻልም ይሁን እንጅ 90 ደቂቃው ግን መበየኑ እና አንዱን ማንገሱ አይቀርም።ኤልክላሲኮ እስካሁን 269 ጊዜ ተካሂዷል። የስፔን አንድነት ምሳሌው ሪያል ማድሪድ 105 ጊዜ በማሸነፍ የበላይነት አለው።

የካታሎኒያ ሀገር የመኾን ዘመናትን የተሻገረ ጥያቄ ማስታገሻው ባርሴሎናም 103 ጊዜ ድል ቀንቶታል። በ52 ጨዋታ ደግሞ ነጥብ ተጋርተዋል።

በመረጃ ምንጭነት ቢቢሲ፣ግል ዶት ኮም እና የስፔን ድረገጾችን ተጠቀምን።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here