በዓመት ከ120 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት በመመደብ የከተማዋን ስፖርት ለማሳደግ እየተሠራ መኾኑን የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር አስታወቀ።

0
126

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 16/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳድር ስፖርት ምክር ቤት 26ኛ ጠቅላላ ጉባኤውን እያካሄደ ነው፡፡ በጠቅላላ ጉባኤው በ2017 ዓ.ም የተከናወኑ ተግባራት እና በቀጣይ ወራት ሊከናወኑ የሚገባቸው ጉዳዮች ተነስተው ውይይት ተደርጎባቸዋል።

በጉባኤው ላይ የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው፣ በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፉ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሞላ ሁሴን፣ የባሕር ዳር ከተማ አስተዳድር ምክትል ከንቲባ አስሜ ብርሌ፣ የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳድር ከፍተኛ አመራሮች፣ የክፍለ ከተማ፣ የቀበሌ አመራሮች እና የስፖርት ምክር ቤት አባላት ተሳትፈዋል፡፡

በጉባኤው ላይ የተገኙት የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው ለስፖርቱ ቤተሰቦች የእንኳን ደህና መጣችሁ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል። የጣናው ሞገድ ባሕር ዳር ከነማ ከባሕር ዳር እንቁነት አልፎ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆኗል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ከተማ አሥተዳድሩ በዓመት ከ120 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት በመመደብ የከተማዋን ስፖርት ለማሳደግ እየሠራ ስለመኾኑም ገልጸዋል። መንግሥት ከሚመድበው በጀት በተጨማሪ ማኅበረሰባዊ ድጋፎችም ተጠናክረው መቀጠል እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡

የስፖርት ምክር ቤት ጉባኤዎች ለከተማዋ ስፖርት እድገት መሠረት ስለመኾናቸውም አመላክተዋል። ስፖርት ለዘላቂ ሰላም እና አብሮነት ያለው ፋይዳም የጎላ ነው ብለዋል።

የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ወጣቶች እና ስፖርት መምሪያ ኀላፊ ቶማስ ታምሩ ስፖርት ለሀገር ኢኮኖሚያዊ እድገት ትልቅ አስተዋጽኦ ያለው በመኾኑ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል፡፡

ስፖርት ትውልድን በአካልም ኾነ በአዕምሮ በጥሩ ሥነ ምግባር የመገንቢያ መሳሪያ በመኾኑ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች በየክፍለ ከተሞች በስፋት እንዲሠሩ ጥረት እየተደረገ መኾኑን ኀላፊው አብራርተዋል፡፡

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here