ባሕር ዳር: ሚያዚያ 08/2017 ዓ.ም (አሚኮ) 9ኛው መላ የደቡብ ወሎ ዞን ስፖርቶች ሻምፒዮና ውድድር ተጠናቅቋል፡፡ ከመጋቢት 26/2017 ዓ.ም ጀምሮ ለ11 ቀናት በቆየው ስፖርታዊ ውድድር 24 ወረዳዎች ተሳትፈውበታል፡፡ አዘጋጁ ደሴ ከተማ 2 ሺህ 500 አትሌቶች እና ልኡካንን አስተናግዷል፡፡
13 ዓይነት የስፖርት ውድድሮች የተደረጉ ሲኾን እግር ኳስ፣ መረብ ኳስ፣ እጅ ኳስ፣ አትሌቲክስ፣ ፓራ ለምፒክ፣ ቼዝ፣ ጠረጴዛ ቴኒስ፣ ዳርት፣ ካራቴ፣ ውሹ እና ክብደት ማንሳት ይጠቀሳሉ። የተንታ አትሌቲክስ ክለብ አትሌት አብዱ ዋሴ በ3 ሺህ እና በ1 ሺህ 500 ሜትር ውድድር ተሳትፎ አሸንፏል።
የ5 ሺህ ሜትር ሯጭነት ህልም ያለው አብዱ ውድድሩ ተግቶ ለመሥራት እንዳነሳሳው ገልጿል።
ሌላኛው አትሌት ሞአዝ አስማረ በመላ ደቡብ ወሎ ውድድር ተሳትፎ በ8 ሺህ እና 1 ሺህ 500 ወርቅ እና ብር አግኝቷል። በመላ አማራ ጨዋታዎች በ800 እና በ1 ሺህ 500 ሜትር ለመወዳደር ልምምዱን ጀምሯል። በዞኑ ከሌሎች ወረዳዎች ስፖርተኞች ጋር በመወዳደራቸው ራሳቸውን መለካታቸውን እና ማኅበራዊ ግንኙነትም መፍጠራቸውንም ተናግሯል።
በመላ አማራ ጨዋታዎችም ለማሸነፍ ከወዲሁ ቅድመ ዝግጅት እያደረገ መኾኑን ለአሚኮ ገልጿል። የቦረና ወረዳ ወጣቶች እና ስፖርት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ወንደወሰን ኡመር በሰላም ችግር ምክንያት ስፖርታዊ እንቅስቃሴ በመቋረጡ ወጣቶች አልባሌ ቦታ ይውሉ እንደነበር ገልጸዋል። ወጣቶች ውድድሩ በመከናወኑ ደስተኛ መኾናቸውን አይተናል ነው ያሉት። ”ስፖርት ለሰላም – ሰላም ለስፖርት” በሚል መሪ ሀሳብ የተደረገው ውድድር ሰላማዊ እንደነበርም ጠቅሰዋል።
ወረዳቸው በእጅ ኳስ አሸናፊ ሲኾን የጸባይ ዋንጫ ተሸላሚም መኾኑን ኀላፊው ገልጸዋል። ለመላ አማራ ውድድርም አትሌቶችን ማስመረጡን ገልጸዋል። የደቡብ ወሎ ዞን አሥተዳደር ወጣቶች እና ስፖርት መምሪያ ኀላፊ ጀማል ሞላ በውድድሩ በፓራ ለምፒክ ደላንታ መሪነቱን ሲይዝ፣ ደሴ ዙሪ እና ቦረና ወረዳ ሁለተኛ እና ሦስተኛ ደረጃ ማግኘታቸውንገልጸዋል።
መስማት በተሳናቸው ደላንታ፣ ቦረና እና ተንታ ወረዳዎች ከአንድ እስከ ሦስት ደረጃዎችን እንደያዙ ተናግረዋል። በዘመናዊ የኦሎምፒክ ስፖርት ውድድሮችም ተንታ፣ አልብኮ እና ኩታበር ወረዳዎች ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ደረጃን ማግኘታቸውን ገልጸዋል። በፓራ ለምፒክ፣ መስማት በተሳናቸው እና በኦሎምፒክ ደሴ ዙሪያ፣ ወረባቦ እና ቦረና እንደ ቅደም ተከተላቸው የጸባይ ዋንጫን ወስደዋል።
ስፖርታዊ ውድድሩ ቤተሰባዊ ፍቅርን እና የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን ያጠናከረ ነበር። ስፖርቱን የደሴን ነዋሪ ጨምሮ በርካታ ሕዝብ ተከታትሎታልም ብለዋል። ውድድሩ የሕዝብን ሥነ ልቦና በማሳደግ፣ በማነቃቃት እና የሕዝብ ለሕዝብ ግንነኙነትንም የማጠናከር ሚና እንደነበረው ነው አቶ ጀማል የገለጹት፡፡
ከቡና እና ሸንኮራ አገዳ ሻጮች ጀምሮ ለበርካቶች የሥራ ዕድል የፈጠረ እንደነበርም በመጥቀስ ለከተማው ማኅበረሰብም የምጣኔ ሃብት መነቃቃት እንደፈጠረም ነው የተናገሩት፡፡ የዞኑ ስፖርታዊ ውድድሮች በሰላም ተጠናቋል ያሉት አቶ ጀማል የኅብረተሰቡ ትብብር እና ሰላማዊነትንም አንስተው አመስግነዋል፡፡
ከሚያዝያ 21/2017 ዓ.ም ጀምሮ በሚካሄደው የመላ አማራ ዘመናዊ ስፖርቶች ሻምፒዮና የሚሳተፉ 350 ስፖርተኞም መመረጣቸውንም ገልጸዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!