መሪው ኢትዮጵያ መድን ከወራጅ ቀጣናው ለመውጣት ከሚታገለው አዳማ ከተማ ጋር ዛሬ ይፋለማሉ።

0
120

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 08/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ በሚደረገው የ25ኛ ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ የደረጃ ሰንጠረዡ መሪ ኢትዮጵያ መድን ከወራጅ ቀጣናው ለመውጣት ከፍተኛ ትግል እያደረገ ካለው አዳማ ከተማ ጋር ይገናኛል። ይህ ጨዋታ ለሁለቱም ቡድኖች እጅግ ወሳኝ ሲኾን ከፍተኛ ፉክክር እንደሚጠበቅበት ተገምቷል።

ኢትዮጵያ መድን በዋንጫ ፉክክሩ ያለውን የበላይነት ለማስቀጠል እና ከተፎካካሪዎቹ ያለውን የነጥብ ልዩነት ለማስፋት ይህንን ጨዋታ በድል ማጠናቀቅ ይፈልጋል። በተለይም ባሕር ዳር ከተማ እና ወላይታ ድቻ ነጥብ በመጣላቸው መድን የነጥብ ልዩነቱን ለማስፋት የሚችልበት ወርቃማ እድል አግኝቷል።

በሌላ በኩል አዳማ ከተማ በዚህ ጨዋታ ውጤት ለማግኘት እና ከላዩ ካለው ሀዋሳ ከተማ ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ለማጥበብ ከፍተኛ ጥረት ያደርጋል። በመጨረሻው ጨዋታ የተከላካይ ክፍሉ ቁልፍ ተጫዋቾች በጉዳት ምክንያት የተዳከመው መድን፣ በረመዳን የሱፍ መመለስ እፎይታን አግኝቷል።

በአንጻሩ አዳማ ከተማ ባለፉት አራት ጨዋታዎች ድል ሳይቀናው የቀረ ሲኾን የወጥነት ችግር የሚታይበት የተከላካይ ክፍሉ ከመድኑ ጠንካራ የፊት መስመር ጋር የሚኖረው ፍልሚያ ፈታኝ ሊኾንበት ይችላል። በአጠቃላይ ይህ ጨዋታ በሁለት የተለያዩ ዓላማዎች የሚፋለሙ ቡድኖች በመኾናቸው ከፍተኛ ፉክክር እና ያልተጠበቀ ውጤት ሊያስከትል እንደሚችል ይጠበቃል።

በሁለቱ ቡድኖች መካከል ያለው የቀድሞ ታሪክ እንደሚያሳየው አዳማ ከተማ በ23 ጨዋታዎች ሰባት ጊዜ በማሸነፍ የተሻለ ክብረ ወሰን ያለው ቢኾንም የዛሬው ጨዋታ ግን ፍጹም የተለየ ሊኾን ይችላል ተብሎ ነው የሚጠበቀው። በሌላ የዛሬ ጨዋታ ድሬዳዋ ከተማ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ ይጫወታሉ። በደረጃ ሰንጠረዡ በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኙት የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ደረጃቸውን ለማሻሻል የሚከናወን ፍልሚያ ነው።

ድሬዳዋ ከተማ በ11 ጨዋታዎች ባገኙት ውጤት መጠነኛ እፎይታን ያገኙ ይመስላሉ። በአዳማ ላይ ያገኙት ድል እና በመጨረሻው ጨዋታ ነጥብ መጋራታቸው ለውጥ አምጥቷል። ሆኖም ከ ወራጅ ቀጣና ስጋቱ ገና አልወጡም። ከዚህ በፊት በተከታታይ ግብ ማስቆጠር ተስኗቸው የነበሩት ብርቱካናማዎቹ በቅርብ ጨዋታዎቻቸው የማጥቃት አቅማቸው መሻሻሉን አሳይተዋል።

ኢትዮ ኤሌክትሪክ በ29 ነጥብ 12ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ቡድኑ በመጀመሪያው ዙር ጥሩ የነበረ ቢኾንም ቀስ እያለ ብቃታቸው ቀንሷል። በቅርብ ጨዋታዎች ሽንፈት እና አቻ ውጤትም አስመዝግበዋል።

የፊት መስመር ጥንካሬያቸውም እንደቀድሞው አለመኾኑ ባደረጓቸው ጨዋታዎች መረዳት ይቻላል።

ሁለቱ ቡድኖች እስካኹን እርስ በእርስ 17 ጊዜ ተገናኝተዋል፤ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ስድስት፣ ድሬዳዋ አራት ጊዜ አሸንፈዋል። ሰባት ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት ነው የተጠናቀቁት።

በምሥጋናው ብርሃኔ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here