3ኛው ኢትዮጵያ ታምርት የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ሚያዝያ 19/ 2017 ዓ.ም ይካሄዳል።

0
220

አዲስ አበባ:ሚያዝያ 07/2017 ዓ.ም (አሚኮ) 3ኛው ኢትዮጵያ ታምርት የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ሚያዝያ 19/ 2017 ዓ.ም ይካሄዳል። በዚህ ውድድር ከ34 ክለቦች እና ተቋማት የተውጣጡ ከ600 በላይ አትሌቶች ተሳታፊ እንደሚኾኑም ይጠበቃል።

ይህ ውድድር የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉን ችግሮች ለመፍታት እና ዘርፉን ለማሳደግ የተጀመረውን የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ለማስተዋወቅ የጎላ ሚና እንደሚኖረው የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ገልጿል።

የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ አበባ ታመነ ሩጫው የሀገር ውስጥ አምራች ኢንዱስትሪዎችን ማስተዋወቅ እና የማምረት አቅማቸውን የማሳየት ዕድል ይፈጥራል ብለዋል። ጤናማ ፣ አምራች ዜጋን የመፍጠር እና ዕድል ላላገኙ አትሌቶች የውድድር ዕድል የመፍጠር ዓላማ እንዳለውም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የውድድር እና ተሳትፎ ዳይሬክተር አስፋው ዳኘ የኢንደስትሪ ሚኒስቴር በየዓመቱ የሚያካሂደው የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ውድድር ለአትሌቲክስ ስፖርት ልማት ከፍተኛ ሚና ያለው መኾኑን ተናግረዋል። ይህ ውድድር በስኬት እንዲካሄድ ፌዴሬሽኑ አስፈላጊውን ድጋፍ እና ክትትል ያደርጋል ብለዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አትሌት መልካሙ ተገኝ ውድድሩ የውድድር ዕድል ላላገኙ አትሌቶች ዕድል እንዲያገኙ የማድረግ ሚና አለው ነው ያሉት።

ይህ ውድድር በቀጣይ እያደገ እንዲሄድ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ጭምር ታዋቂ እንዲኾን የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የበኩሉን እንደሚወጣ ተናግረዋል።

በዚህ ውድድር ከ1 እስከ 10 ለሚወጡ አትሌቶች የገንዘብ ሽልማት እንደሚበረከት ተገልጿል።

1ኛ ለሚወጡ 300 ሺህ ብር

2ኛ ለሚወጡ 200 ሺህ ብር

3ኛ ለሚወጡ 100ሺህ ብር ሽልማት ይበረከታል።

3ኛው የኢትዮጵያ ታምርት የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ውድድር መነሻ እና መድረሻውን መስቀል አደባባይ በማድረግ ሚያዝያ 19/2017 ዓ.ም እንደሚካሄድ አዘጋጆች እና ባለድርሻ አካላት በሰጡት የጋራ መግለጫ አስታውቀዋል።

ዘጋቢ፦ ባዘዘው መኮንን

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here