ባሕር ዳር:ሚያዝያ 07/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የሩብ ፍጻሜ የመልስ ጨዋታ ዛሬ ምሽት ቦሩሲያ ዶርትሙንድ በሜዳው ሲግናል ኢድና ፓርክ ባርሴሎናን ያስተናግዳል። ቦሩሲያ ዶርትሙንድ በአውሮፓ ውድድሮች ባርሴሎናን አንድም ጊዜ ማሸነፍ አልቻለም አጠቃላይ ስድስት ጨዋታ አድርገው ሁለቱን አቻ ሲለያዩ በአራቱ ደግሞ ሽንፈት ገጥሟቸዋል።
በዚህ ጨዋታ ማሸነፍ ካልቻሉ በአውሮፓ ፉክክር በአንድ ተጋጣሚ ላይ ረጅሙን ያለድል ጉዞ ያስተናግዳሉ፤ ይህም ከ1966 እስከ 1999 ከሬንጀርስ ጋር በነበራቸው ሰባት ጨዋታዎች ያለድል መቆየት ጋር እኩል ይኾናል። ባርሴሎና በዚህ የውድድር ዓመት በሻምፒዮንስ ሊግ ከጀርመን ቡድኖች ጋር ያደረጋቸውን ሦስት ጨዋታዎች በሙሉ አሸንፏል። ባየርን ሙኒክን 4ለ1 እና ቦሩሲያ ዶርትሙንድን 3ለ2 እና 4ለ0 ማሸነፍ ችሏል።
ከዚህ የውድድር ዓመት በፊት ባርሴሎና በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ከጀርመን ቡድኖች ጋር በተከታታይ አምስት ጨዋታዎችን የተሸነፈ ሲኾን በአጠቃላይ 19ለ2 በኾነ የግብ ልዩነት ተረቷል። ቦሩሲያ ዶርትሙንድ በአውሮፓ ውድድሮች በሜዳው ከባርሴሎና ጋር ባደረጋቸው ሦስት ጨዋታዎች ያለድል ነው የተለያየው። ሁለት አቻ አንድ ጊዜ ደግሞ ተሸንፏል።
ዶርትሙንድ በመጀመሪያው ጨዋታ አራት ግቦች ተቆጥሮበት መሸነፉ የዛሬውን ጨዋታ ያከብድበታል። ነገር ግን ከዚህ በፊት መሰል ውጤቶችን የቀለበሱ ቡድኖች መኖራቸው የጀርመኑ ክለብ ተስፋ እንዳይቆርጥ ያደርገዋል። ባርሴሎና በ2016/17 የውድድር ዘመን በጥሎ ማለፍ 1ኛ ዙር ጨዋታ በፓሪስ ሴንት ዠርሜንን 4ለ0 ተሸንፎ ሁለተኛው ጨዋታ 6ለ1 ያሸነፈበት ጨዋታ ለዚህ አብነት ነው።
የባርሴሎናዎቹ ሮበርት ሌዋንዶቭስኪ እና ራፊንሃ በዚህ ውድድር ድንቅ ጊዜ እያሳለፉ ነው። ሉዋንዶስኪ 30 ዓመቱን ከሞላ በኋላ በ59 የሻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታዎች 60 ጎሎችን አስቆጥሯል፤ ከእሱ በላይ በዚህ የዕድሜ ክልል በውድድሩ ብዙ ግቦችን ያስቆጠረው ክርስቲያኖ ሮናልዶ ብቻ ነው። በ74 ጨዋታዎች 68 ግቦችን አስመዝግቧል።
ራፊንሃ ደግሞ በዚህ የውድድር ዓመት በ11 የሻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታዎች በቀጥታ በ19 ጎሎች ላይ ተሳትፏል፤ 12 ግቦችን ሲያስቆጥር ሰባት ኳሶችን አመቻችቶ አቀብሏል። በሌላ የዛሬ የሩብ ፍጻሜ የመልስ ጨዋታ ምሽት አስቶን ቪላ በሜዳው ቪላ ፓርክ ፓሪስ ሴንት ዠርሜንን ያስተናግዳል። አስቶን ቪላ በኡናይ ኤመሪ ስር በአውሮፓ ውድድሮች ከፈረንሳይ ቡድኖች ጋር ባደረጋቸው አራት ጨዋታዎች ሦስቱን ተሸንፏል፤ ሦስቱም ሽንፈቶች በተከታታይ የመጡ ናቸው።
ብቸኛ ድላቸውን ያስመዘገቡት በቪላ ፓርክ በተደረገው ጨዋታ ሲኾን በ2024 በኮንፈረንስ ሊግ ሊልን 2ለ1 አሸንፈዋል። ፓሪስ ሴንት ዠርሜን በሻምፒዮንስ ሊግ የጥሎ ማለፍ የመጀመሪያ ጨዋታ በሁለት እና ከዚያ በላይ በኾነ የግብ ልዩነት ካሸነፈባቸው ሰባት አጋጣሚዎች ሦስቱ ላይ ከውድድሩ ተሰናብቷል።
በዚህ ጨዋታ ማለፍ ተስኗቸው ከቀሩ ደግሞ ከመጀመሪያው ጨዋታ የሁለት እና ከዚያ በላይ የግብ ልዩነት ይዘው በሻምፒዮንስ ሊግ የጥሎ ማለፍ ውድድር ከሌሎች በበለጠ አራት ጊዜ የተሰናበቱ በሚል ታሪክ ይጽፋቸዋል።ፓሪስ ሴንት ዠርሜን በአውሮፓ ውድድሮች በእንግሊዝ ቡድኖች ሜዳ ባደረጋቸው 17 ጨዋታዎች አራት ጊዜ ብቻ ነው ያሸነፈው። አራት ጊዜ አቻ ሲወጣ ዘጠኝ ጊዜ ደግሞ ተሸንፏል።
ከእነዚህ ድሎች አንዱ በቅርቡ ሊቨርፑልን 1ለ0 ያሸነፈበት ጨዋታ ነበር። ይህም በእንደዚህ አይነት ጨዋታዎች በተከታታይ የደረሰባቸውን አራት ሽንፈቶች ያስቆመም ነበር። ከ2022/23 የውድድር ዓመት ጀምሮ የአስቶን ቪላው አለቃ ኡናይ ኤመሪ በአውሮፓ ዋንጫ በሜዳቸው በ13 ጨዋታዎች አንድ ጊዜ ብቻ የተሸነፉት።
11 ጊዜ አሸንፈዋል አንድ ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። ብቸኛ ሽንፈታቸው በ2024 በኮንፈረንስ ሊግ የፍጻሜ ግማሽ የመጀመሪያ ጨዋታ ከኦሊምፒያኮስ ጋር በሜዳቸው 4ለ2 የተሸነፉበት ነበር። ፓሪስ ሴንት ዠርሜን በዚህ የውድድር ዓመት በሻምፒዮንስ ሊግ አምስት እና ከዚያ በላይ ግቦች ላይ በቀጥታ የተሳተፉ አራት የተለያዩ ተጫዋቾች አሉት።
እነሱም ኡስማን ዴምቤሌ ዘጠኝ ግብ፣ አሽራፍ ሃኪሚ እና ብራድሌይ ባርኮላ እያንዳንዳቸው ግቦችን ሲያስቆጥሩ፣ ዴዚሬ ዱዌ አምስት ግቦችን አስቆጥሯል። የአስቶን ቪላው ሞርጋን ሮጀርስ በዚህ የውድድር ዓመት በሻምፒዮንስ ሊግ ለቡድኑ ስድስት ግቦች ላይ በቀጥታ ተሳትፏል፤ አራት ግቦች ሲያስቆጥር፣ ሁለት ኳሶችን አመቻችቶ ሰጥቷል።
የፓሪስ ሴንት ዠርሜኑ አማካይ ጆአዎ ኔቭስ በዚህ የውድድር ዓመት በሻምፒዮንስ ሊግ ከማንኛውም አማካይ ተጫዋች የበለጠ ከፍተኛ ሙከራዎችን አድርጓል። ዩሪ ቲዬለማንስ በዚህ የውድድር ዓመት በአስቶን ቪላ በሻምፒዮንስ ሊግ ብዙ የተሳካ ኳሶችን በማቀበል፣ የተከላካይ መስመርን ሰብረው የሚያልፉ ኳሶችን በማቀበል እንዲኹም ኳስን መልሶ በመቆጣጠር እና የተሳካ የመከላከል ሙከራዎችን በማድረግ ቀዳሚ ተጫዋች ነው።
ጨዋታዎቹ ምሽት አራት ሰዓት ይጀምራሉ።
በምሥጋናው ብርሃኔ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን