ዛሬ በኢትዮጵያ ፕምዬር ሊግ ተጠባቂ ጨዋታዎች ይካሄዳሉ።

0
123

ባሕር ዳር:ሚያዝያ 06/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ ፕሪምዬር ሊግ 25ኛ ሳምንት ዛሬም ቀጥሎ ሲካሄድ ሦስት ጨዋታዎች ይካሄዳሉ።

ረፋድ 3:30 ቅዱስ ጊዮርጊስ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሚያደርጉት ጨዋታ ቀዳሚው ነው። ከወትሮው በተለየ መንገድ በደካማ አቋም ላይ የሚገኘው ቅዱስ ጊዮርጊስ ድል ከራቀው ቆይቷል። በነጥብ ተቋራራቢ የኾኑት ቡድኖች ረፋድ ላይ የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል።

ቀን 9:00 ደግሞ ሲዳማ ቡና ከባሕር ዳር ከተማ ጋር ይጫወታሉ። ሁለቱም ቡድኖች በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ በሁለተኛ እና በአራተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ መኾኑ እና ውጤታቸውም ተቀራራቢ በመኾኑ ጨዋታው ከፍተኛ ትኩረትን እንዲስብ አድርጎታል።

የጣናሞገዶቹ በጥሩ ብቃት ላይ ሲኾን ባለፉት ጨዋታዎች አብዛኞቹን በድል አጠናቅቀዋል። ቅዱስ ጊዮርጊስን 4ለ1፣ ሀድያ ሆሳዕናን 1ለ0፣ ኢትዮጵያ ቡናን 2ለ0 ሲያሸንፍ ከፋሲል ከነማ እና ከሽረንዳስላሴ ጋር ያደረጋቸው ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ማጠናቀቁ የቡድኑን ጥንካሬ ጨቋሚ ምልክቶች ናቸው።

የባሕር ዳር ከተማ የማጥቃት እና የመሐል አማካይ ክፍሎች ጠንካራ ናቸው። በደረጃ ሰንጠረዡም በ37 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። ሁለቱ ቡድኖች እስካሁን 12 ጊዜ የተገናኙ ሲኾን ባሕር ዳር አራት ጊዜ ሲያሸንፍ ሲዳማ ቡና ስድስት ጊዜ አሸንፏል። ሌሎቹ ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት ነው የተጠናቀቁት።

የሲዳማ ቡና የተከላካይ ክፍሉ ጠንካራ መኾን ለባሕር ዳር ከተማ አጥቂዎች ፈታኝ ሊኾን እንደሚችል ይጠበቃል። ሲዳማ ቡና በደረጃ ሰንጠረዡ በ36 ነጥብ አራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። በደረጃ ላይ ለውጥ የሚያመጣው ጨዋታ ብርቱ ፉክክር እንደሚደረግበት ይጠበቃል። የዕለቱ የመጨረሻ ጨዋታ በሀዋሳ ከተማ እና በወላይታ ዲቻ መካከል ይካሄዳል። ጨዋታው ምሽት 12:00 ሲል ይደረጋል።

የደረጃ ሠንጠረዡን ኢትዮጵያ መድን በ45 ነጥብ ሲመራ ዛሬ ጨዋታ ያለባቸው ባሕር ዳር ከተማ እና ወላይታ ዲቻ በጎል ክፍያ ተበላልጠው በ37 ነጥብ ሁለተኛ እና ሦስተኛ ደረጃ ተቀምጠዋል።

በምሥጋናው ብርሃኔ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here