በኢትዮጵያ ፕሪምየርሊግ ዛሬ ሁለት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።

0
112

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 01/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በ24ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ እና ሀዋሳ ከተማ 9:00 ሰዓት ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ክለብ ጥሩ ጊዜ እያሳለፈ አይደለም። ቡድኑ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ባደረጋቸው አምስት ጨዋታዎች ሦስት ሽንፈቶችን አስተናግዷል።

ብቸኛውና የሚያበረታታው ውጤት ከዚህ ቀደም አርባምንጭ ከተማን 2ለ1 ማሸነፋቸው ነው። በሌላ በኩል የሀዋሳ ከተማ ክለብ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተሻለ እንቅስቃሴ እያሳየ ይመስላል። ምንም እንኳን በቅርቡ ከኢትዮጵያ መድን ጋር ባደረጉት ጨዋታ ቢሸነፉም መቀሌ 70 አንደርታን በ5ለ2 ማሸነፋቸው ቡድኑ በመጠኑም ቢኾንም መነሳሳት ላይ መኾኑን ያሳያል።

ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ያደረጉት ሌላው ጨዋታ ያለ ግብ በአቻ ውጤት መጠናቀቁም ተጋጣሚያቸውን ምን ያህል እንደተፈታተኑ ያሳያል። ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ እና ሀዋሳ ከተማ መካከል ያለውን የቀድሞ የጨዋታ ታሪክ ስንመለከት ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ በአስር ጨዋታዎች አሸንፏል። ሀዋሳ ከተማ በበኩሉ በአምስት ጨዋታዎች ነው ማሸነፍ የቻለው።

አራት ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት ተጠናቅቀዋል። ይህ የሚያሳየው ሁለቱ ቡድኖች ለረዥም ጊዜ ጠንካራ የፉክክር ታሪክ እንዳላቸው ነው። በሌላ ጨዋታ 12 ሰዓት ላይ ሽረ እንዳስላሴ እና ሲዳማ ቡና ይጫወታሉ። የሁለቱን ቡድኖች የቅርብ ጊዜ ውጤቶቻቸው ስንመለከት ሽረ እንዳስላሴ በተከታታይ ባደረጋቸው ጨዋታዎች የተሻለ እንቅስቃሴ እያሳየ አይደለም።

ካለፉት አምስት ጨዋታዎች አንዱን ብቻ ያሸነፈ ሲኾን ሦስት ሽንፈቶችን እና አንድ አቻ ውጤት አስመዝግቧል። በተለይም በቅርብ ካደረጋቸው ጨዋታዎች ውስጥ ከባሕር ዳር ከተማ ጋር ያለግብ አቻ መውጣቱ የሚያበረታታ ቢኾንም በአጠቃላይ የግብ ማስቆጠር ችግር ይታይበታል። በሌላ በኩል ሲዳማ ቡናም በቅርብ ጊዜያት ወጥ አቋም ማሳየት አልቻለም።

ካለፉት አምስት ጨዋታዎች በአራቱ አቻ በአንድ ጨዋታ ደግሞ ተሸንፏል። ቡድኑ ብዙ ጊዜ ሽንፈት ባይገጥመውም በተደጋጋሚ ነጥብ መጣሉ ከመሪዎች እንዲርቅ አድርጎታል።

በምሥጋናው ብርሃኔ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here