ፋሲል ከነማ ዛሬ ወሳኝ ጨዋታውን ያደርጋል።

0
116

ባሕር ዳር: መጋቢት 25/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 23ኛ ሳምንት ዛሬ ሦስት ጨዋታዎች ይደረጋሉ። ፋሲል ከነማ በሰንጠረዡ ግርጌ ላይ የሚገኘው ወልዋሎ አዲግራት ይገጥማል። ወልዋሎዎች በውድድር ዓመቱ ደካማ ውጤት እያስመዘገቡ የሚገኙ ሲኾን ከወራጅ ቀጣናው ለመውጣት ከፍተኛ ትግል ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።

ወልዋሎዎች የተወሰኑ ተጫዋቾቻቸው በጉዳት እና በቅጣት ምክንያት በዛሬው ጨዋታ እንደማይሰለፉ ታውቋል። ፋሲል ከነማዎች በ22ኛው ሳምንት መቻልን በማሸነፍ ጥሩ ሞራል ላይ የሚገኙ ሲኾን በዛሬው ጨዋታ ሙሉ ነጥብ በማግኘት ከሰንጠረዡ አጋማሽ ለመሻገር ወሳኝ ጨዋታን ነው የሚያደርጉት።

ከዚህ ቀደም የግብ ዕድሎችን የመፍጠር ክፍተት የነበረበት የአሠልጣኝ ውበቱ አባተው ቡድን በማጥቃቱ ረገድ በዛሬው ጨዋታ መሻሻል ይጠበቅበታል። ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ አምስት ጊዜ የተገናኙ ሲኾን ፋሲል ከነማ ሦስት ጊዜ አሸንፏል። ሁለቱ ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት ተጠናቅቀዋል።

ወልዋሎዎች እስካኹን ፋሲል ከነማን ማሸነፍ አልቻሉም። ይህ ጨዋታ ለሁለቱም ቡድኖች ወሳኝ ሲኾን በተለይ ወልዋሎዎች ከወራጅ ቀጣናው ለመውጣት ከፍተኛ ትግል ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል። ጨዋታው ጠዋት 3 ሰዓት 30 ይካሄዳል። በሌላው ወሳኝ ጨዋታ በወራጅ ቀጣናው ስጋት ላይ የሚገኙት ሀዋሳ ከተማዎች ከሊጉ መሪ ኢትዮጵያ መድን ጋር ነው የሚገናኙት።

ሀዋሳ ከተማ በ20 ነጥቦች 15ኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ሲኾን ከወራጅ ቀጣናው ለመውጣት ከፍተኛ ትግል እያደረገም ነው። በቅርቡ የአሠልጣኝ ለውጥ ያደረገው ቡድኑ በአሠልጣኝ ሙልጌታ ምሕረት እየተመራ የተሻለ እንቅስቃሴ እያሳየ ነው። ይኹን እንጂ ቁልፍ ተጫዋቾች በጉዳት እና በቅጣት ምክንያት ለጨዋታው አይደርሱም። በተለይ የክለቡ ወሳኝ ተጫዋች አሊ ሱሌይማን አለመሰለፉ ለክለቡ መጥፎ ዜና ነው።

በሌላ በኩል ኢትዮጵያ መድን በ41 ነጥቦች በሊጉ መሪነቱን ይዟል። ለዋንጫውም ተፎካካሪ ነው። ጠንካራ የመከላከል እና የማጥቃት ብቃት ያለው ቡድንም ነው። ወጣቱ መሀመድ አበራ ለኢትዮጵያ መድን ጥሩ እንቅስቃሴን እያሳየ ይገኛል። ሁለቱ ቡድኖች ሲገናኙ ሀዋሳ ከተማ የተሻለ ውጤት አለው።

ይህ ጨዋታ ለሁለቱም ቡድኖች ወሳኝ ነው። ሀዋሳ ከተማ ከወራጅ ቀጣናው ለመውጣት፣ ኢትዮጵያ መድን ደግሞ መሪነቱን ለማጠናከር ይጫወታሉ። ጨዋታው ከፍተኛ ፉክክር ይኖረዋል ተብሎም ይጠበቃል። ጨዋታው 12 ሰዓት ላይ ይጀመራል። ሦስተኛው ጨዋታ ወላይታ ድቻ እና መቐለ 70 እንደርታ በ9:00 የሚገናኙበት ነው።

ወላይታ ድቻ በቅርብ ጊዜያት ጥሩ ብቃት እያሳየ የሚገኝ ሲኾን በተለይም የተከላካይ መስመሩ ተሻሽሏል። በሁለተኛው ዙር በተካሄዱት ሦስት ጨዋታዎች ሙሉ ነጥብ በማግኘት ከመሪዎቹ ጎራ ተቀላቅሏል። ተከላካዩ መልካሙ ቦጋለ ከጉዳት አገግሞ ወደ ልምምድ መመለሱ ለቡድኑ ትልቅ አቅም ይፈጥራል።

መቐለ 70 እንደርታ ከወራጅ ቀጣና ለመራቅ ይህን ጨዋታ ማሸነፍ ይኖርበታል። ተመስገን በጅሮንድ፣ ሔኖክ አንጃው እና ያሬድ ብርሃኑ በጉዳት ምክንያት ከጨዋታው ውጭ እንደኾኑም ታውቋል። ሁለቱ ቡድኖች ሲገናኙ መቐለ 70 እንደርታ የተሻለ ውጤት አለው። ሁለቱም ቡድኖች ወሳኝ ጨዋታን እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።

በምሥጋናው ብርሃኔ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here