ባሕር ዳር፡ መጋቢት 24/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከአህጉራዊ ጨዋታዎች እረፍት በኋላ ሲመለስ 23ኛ ሳምንት መረሐ ግብሩን ዛሬ በሚደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ይጀምራል። ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሀድያ ሆሳዕና 9:00 ሰዓት እና አዳማ ከተማ ከድሬዳዋ ከተማ ምሽት 12 ሰዓት ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
በተቀራራቢ ደረጃ የሚገኙት ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ሀድያ ሆሳዕና ዛሬ ለአሸናፊነት ይፋለማሉ። ቅዱስ ጊዮርጊስ በ30 ነጥብ ስድስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ሀድያ ሆሳዕና በ32 ነጥብ አምስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ሁለቱም ቡድኖች በቅርብ ጨዋታዎች ጥሩ ውጤት አላስመዘገቡም። የዛሬው ጨዋታም ወደ ድል ለመመለስ የሚደረግ ፉክክር ነው።
ቅዱስ ጊዮርጊስ ሻይዱ ሙስጠፋ እና አብዱልሀዚዝ ቶፊቅን በጉዳት አያሰልፍም። ሀዲያ ሆሳዕና ደግሞ መለሰ ሚሻሞ፣ ጫላ ተሺታ፣ በረከት ወንድሙ እና ሄኖክ አርፊጮን በጉዳት ምክንያት ከጨዋታው ውጭ ኾነው ነው ጨዋታውን የሚያደርገው።
ሁለቱ ቡድኖች እስካሁን 11 ጊዜ ተገናኝተዋል። ቅዱስ ጊዮርጊስ አራት ጊዜ ሲያሸንፍ ሀዲያ ሆሳዕና በሦስቱ ድል አድርጓል። በቀሪው አቻ ተለያይተዋል። በሌላ ጨዋታ በወራጅ ቀጣናው ስጋት ላይ የሚገኙት አዳማ ከተማ እና ድሬዳዋ ከተማ የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው። አዳማ ከተማ በ20 ነጥብ 16ኛ ደረጃ ላይ ነው። ድሬዳዋ ከተማ በ22 ነጥብ 14ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
አዳማ ከተማ በቅርብ ጊዜያት መጠነኛ መሻሻል እያሳየ ነው። ድሬዳዋ ከተማ በበኩሉ ላለፉት 11 ጨዋታዎች ማሸነፍ አልቻለም። በአዳማ ከተማ በኩል የግብ ጠባቂው ዳግም ተፈራ መሰለፉ አጠራጣሪ ነው። በድሬዳዋ ከተማ በኩል ደግሞ መሐመድኑር ናስር በጉዳት ምክንያት በሥብሥቡ አይካተትም።
ሁለቱ ቡድኖች 25 ጊዜያት የተገናኙ ሲኾን አዳማ ከተማ 12 ጊዜ ሲያሸንፍ ድሬዳዋ ከተማ ስድስት ጊዜ አሸንፏል። ሰባት ጊዜ ደግሞ ነጥብ ተጋርተዋል።
በምሥጋናው ብርሃኔ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!