ባሕር ዳር፡ መጋቢት 17/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ብራዚል እና አርጀንቲና ትልቅ የእግር ኳስ ሀገራት ናቸው። በዓለም እግር ኳስ ስማቸው ከመቃብር በላይ የዋለ ኮከቦችን አፍርተዋል። አኹንም በትልልቅ የአውሮፓ ሊጎች እግር ኳስ አፍቃሪያንን ያስጨበጨቡ የሁለቱ ሀገራት ኮከቦች ብዙ ናቸው።
ብራዚል እና አርጀንቲና በዓለም ዋንጫ እና ኮፓ አሜሪካ ውጤታማ ታሪክ አላቸው።
አርጀንቲና ሦስት ጊዜ የዓለም ዋንጫን አሸንፋለች። 16 ጊዜ የደመቀችበት የኮፓ አሜሪካ ዋንጫ ደግሞ በአሕጉሩ ቀዳሚዋ ውጤታማ ሀገር ያደርጋታል።
ብራዚል ደግሞ በዓለም ዋንጫ ቀዳሚዋ ስኬታማ ሀገር ናት። ውድድሩን አምስት ጊዜ ከፍ ስታደርግ፣ ኮፓ አሜሪካን ደግሞ ዘጠኝ ጊዜ አሸንፋለች።
ሁለቱ ሀገራት 115 ጊዜ ተገናኝተዋል። ብራዚል 46፣ አርጀንቲና ደግሞ 43 ጊዜ አሸንፈዋል፤ ቀሪው ነጥብ የተጋሩበት ነው።
ይሄ የእግር ኳስ ውጤታማነታቸው ታዲያ ሁለቱን ሀገራት በእግር ኳሱ ተቀናቃኝ አድርጓቸዋል። ሁለቱ ሀገራት እርስ በእርስ የሚገናኙበት ጨዋታም በእልህ እና ለማሸነፍ ብቻ የሚደረግ ነው።
የተጫዋቾች እና ደጋፊዎች የድጋፍ ስልት የሜዳ ውስጥ ሌላ ገጽታ ኾነው ለዘመናት ቀጥለዋል።
ሁለቱ ሀገራት በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ የተገናኙበት የትናንት ሌሊቱ ጨዋታ በብዙዎች ተጠብቆ በአርጀንቲና አሸናፊነት ተጠናቅቋል። ጨዋታውን የኳታር የዓለም ዋንጫ አሸናፊዋ አርጀንቲና 4ለ1 ነው የረታችው።
ውጤቱን ተከትሎ አርጀንቲና ለ2026 የዓለም ዋንጫ ማለፏን አረጋግጣለች። ነገር ግን ይህ ጨዋታ ለአርጀንቲናውያን የዓለም ዋንጫ ቦታን ከማግኘት በላይም ነው፤ ምክንያቱም ያሸነፉት ብራዚልን ያውም አራት ግብ አስቆጥረው ነውና።
ለብራዚላውያንም ቢኾን ህመሙ የበረታባቸው፣ ሽንፈቱ ያንገበገባቸው ሽንፈቱ ከዓለም ዋንጫ ስለሚያስቀራቸው አይደለም። የተሸነፉት በታሪካዊ ተቀናቃኛቸው ያውም በሰፊ ግብ መኾኑ እንጅ።
ሁለቱ ሀገራት በተገናኙባቸው የተለያዩ ውድድሮች አሸናፊው ጮቤ እየረገጠ፣ ተሸናፊው አንገት እየደፋ የታየባቸው ጊዜያት አልፈዋል። ለጊዜው ደስታ ከነማራዶና እና ሜሲ ቀየ ናት። በእነ ፔሌ እና ሮናልዶ ወገን ግን ጥሩ ነገር የለም።
በአስማማው አማረ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!