ወልድያ: መጋቢት 12/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ስምንተኛው የመላው ሰሜን ወሎ ዞን ዘመናዊ ስፖርት ውድድር በሃራ ከተማ ተጀምሯል። የሰሜን ወሎ ዞን ወጣቶች እና ሰፖርት መመሪያ ኀላፊ አሸናፊ ሰማው በስምንተኛው የመላው ሰሜን ወሎ ዞን ዘመናዊ ስፖርት ዉድድር ከአራት ከተማ አሥተዳደሮች እና ከስድስት ወረዳዎች የተውጣጡ 500 ስፖርተኞች ይሳተፋሉ ብለዋል። ውድድሩም ለአስር ቀናት እንደሚቆይ ተናግረዋል።
ውድድሩ ተቀዛቅዞ የቆየውን ዞናዊ የስፖርት እንቅስቃሴ ለማነቃቃት፣ በመላው አማራ ስፖርታዊ ውድድር ላይ ዞኑን የሚወክሉ ስፖርተኞችን ለመመልመል እና ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት እንደሚያስችል ገልጸዋል። ስፖርት ለሀገር ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ድፕሎማሲያዊ ዕድገት ጉልህ ሚና እንዳለውም ተናግረዋል። ስፖርተኞች መከባበርን፣ በፍቅር አብሮ መኖርን፣ መረዳዳትን፣ ሕግ እና ሥርዓት ማክበርን በቆይታቸው አጎልብተው ከውድድር ባሻገር አብሮነታቸውን እንድያጠናክሩም አሳስበዋል።
የሃራ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ ሙሐመድ ሰኢድ ውድድሩ የአንድነታችን እና የወንድማማችነታችን ብሩህ ማሳያ ነው ብለዋል። ሀራ ከተማ ውድድሩም በማስተናገዷ ደስተኛ መኾናቸውን ተናግረዋል። ተወዳዳሪዎች ቆይታቸው ስኬታማ እንዲኾን መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል። ውድድሩ እስከሚጠናቀቅ አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግም አመላክተዋል።
ውድድሩ የሰሜን ወሎ ዞን ወጣቶች፣ ለሀገራቸው ያላቸውን ፍቅር እና ቁርጠኝነት የሚያሳይ ብሩህ ገጽ ነው ብለዋል። የስፖርቱ መንፈስ፣ ለሰላም እና ለልማት ያለንን ጽኑ ቁርጠኝነት ያጠናክራል ነው ያሉት።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!