ባደጉበት ዓመት ለመውረድ ጫፍ የደረሱ ክለቦች።

0
147

ባሕር ዳር: መጋቢት 09/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የእንግሊዝ ፕርምየር ሊግን ከሌሎች ሊጎች በተለየ ኹኔታ ተመራጭ የሚያደርገው እስከ ውድድር ዓመቱ ፍጻሜ ድረስ ሻምፒዮናው ክለብ፣ በአውሮፓ መድረክ የሚሳተፉ ክለቦች እና ወደታችኛው ሊግ ላለመውረድ የሚጫወቱት ክለቦች የማይታወቁ በመኾናቸው ነበር፡፡

በዘንድሮው የ2024/25 የውድድር ዘመን ግን በተለይ ወደ ታችኛው ሊግ የሚወርዱት ክለቦች እየታወቁ መጥተዋል፡፡ ሳውዝአምፕተን፣ ሌስተር ሲቲ እና ኤፕስዊች ታውን ወደ ፕርምየር ሊጉ በመጡ በዓመታቸው ወደ ታችኛው ፕርምየር ሺፕ የሚወርዱ ክለቦች መኾናቸው የማይቀር ይመስላል።
ሌስተር ሲቲ እና ሳውዝአምፕተን በ2023 ወደ ታችኛው ሊግ በወረዱ በዓመታቸው ወደ ፕሪምየር ሊጉ መመለሳቸው አድናቆትን አስገኝቶላቸው ነበር።

ነገር ግን አሁን እንደገና ወደታች ለመመለስ ጫፍ ደርሰዋል። ከ22 ዓመታት በኋላ ወደ ፕሪምየር ሊጉ የተመለሰው ኤፕስዊች ታውንም በመጣበት ዓመት ወደ ለመደው የታችኛው ሊግ መመለሱ አይቀሬ ይመስላል። ሳውዝአምፕተን በፕሪምየር ሊጉ 29 ጨዋታዎችን አድርጎ ሁለት ጨዋታዎችን ብቻ በማሸነፍ፣ በሦስቱ አቻ በመውጣት እና በ24 ጨዋታዎች ደግሞ በመሸነፍ 34 የግብ ዕዳዎችን ተሸክሞ በዘጠኝ ነጥብ 20ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡

ሌስተር ሲቲ ከ29 ጨዋታዎች በአራቱ አሸንፎ፣ በአምስቱ አቻ ወጥቶ እና በ20 ጨዋታዎች ደግሞ ተሸንፎ፣ በ40 የግብ ዕዳዎች 17 ነጥብ ብቻ በማስመዝገብ በ19ኛ ደረጃ ላይ ወራጅ ቀጣና ውስጥ ተቀምጧል፡፡ ኤፕስዊች ታውን ካደረጋቸው 29 ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው ሦስቱን ብቻ ነው፡፡ በስምንቱ አቻ ሲለያይ 18 ጨዋታዎችን ደግሞ ተሸንፏል። ኤፕስዊች 49 የግብ ዕዳዎች ያሉበት ሲኾን ከ29 ጨዋታዎች የሠበሠበው ነጥብም እንደሌስተር ሲቲ ሁሉ 17 ነው፡፡

17ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ወልቭስ 26 ነጥቦችን ሠብሥቦ ከሌስተር እና ኢፒስዊች በዘጠኝ ነጥብ ከፍ ብሎ ይገኛል። ፕርምየር ሊጉ የሚቀሩት ጨዋታዎችም ዘጠኝ ናቸው። ይህም የሳውዝአፕተን፣ ሌስተር እና ኢፒስዊችን የመትረፍ ዕድል የጠበበ ያደርገዋል። ከዚህ በፊት ከዋንጫው ፉክክር በተጨማሪ ላለመውረድ የሚደረገው ትንቅንቅ የሊጉ ድምቀት ነበር። ዘንድሮ ግን አጓጊ አይደለም። የዋንጫ ፉክክሩም ቢኾንም የተጠናቀቀ እየተባለ ነው፤ ሊቨርፑል ለክብሩ ተቃርቧል በሚል።

ዘጋቢ፡- እሱባለው ይርጋ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here