“የኳሱ ንጉስ”

0
162

ፍኖተ ሰላም፡ መጋቢት 08/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የዳሞት ከነማ እግር ኳስ ክለብ ስም ሲነሳ ስማቸው አብሮ ይነሳል። በአካባቢው ተስጥኦ ያላቸው ወጣቶችን ኮትኩተው በማሳደግ ባለውለታ ናቸው። በኢትዮጵያ እግር ኳስ ትልቅ ቦታ የደረሱ ተጫዋቾች እና አሠልጣኞች ላይ የራሳቸውን አሻራ አሳርፈዋል፤ አሠልጣኝ ዘነበ አሰፋ።

አቶ ዘነበ አሰፋ ዳሞት ከነማ እግር ኳስ ክለብ ከተመሠረተበት ጊዜ አንስቶ ጠንክረው በማሠልጠን በአንድ ዓመት ብቻ ከወረዳ እስከ ክልል በተደረጉ ውድድሮች ሦስት ዋንጫዎችን ለአካባቢው ሕዝብ አስገኝተዋል። በአካባቢው ስፖርት አፍቃሪያን ዘንድ “የእግር ኳሱ ንጉስ” እስከ መባል የደረሱ ስመጥር ናቸው። ተጫዋቾችን በሥነ ምግባር ኮትኩቶ በማሳደግ እና ለሙያው ልዩ ክብር እንዲሰጡ በማድረግ ይታወቃሉ።

አሠልጣኝ ዘነበ አሰፋ ለዳሞት ከነማ እግር ኳስ ክለብ ላበረከቱት አስተዋጽኦ በክለቡ ተጫዋቾች እና በአካባቢው ስፖርት አፍቃሪያን ዕውቅና ተሰጥቷቸዋል። አሠልጣኙ ከሚኮ ጋር በነበራቸው ቆይታ እግር ኳስ ሙያቸው ብቻ ሳይኾን ሕይወታቸውም ጭምር እንደኾነ ተናግረዋል። ለተጫዋቾቸ አሠልጣኝ ብቻ ሳይኾን አባትም ነኝ ሲሉም አክለዋል።

በእሳቸው ስር የመሰልጠን እድል ያገኙትም ትጋት፣ ቁርጠኝነት እና ለዓላማ መጽናት የአቶ ዘነበ መገላጫ ናቸው በማለት ምስክርነት ሰጥተዋቸዋል። የዳሞት ከነማ እግር ኳስ ክለብ ከምስረታው ጀምሮ እስከ ከፍተኛ ሊግ እንዲደርስ የአሠልጣኝ ዘነበ ሚና ግንባር ቀደም እንደነበር ተገልጿል። በዕውቅና መርሐ ግብሩ ላይ በዳሞት ከነማ እና በቡሬ ዳሞት ከነማ እግር ኳስ ክለቦች መካከል የወዳጅነት ጨዋታ የተደረገ ሲኾን ጨዋታው ያለ ጎል ተጠናቅቋል።

በመጨረሻም የፍኖተ ሰላም ከተማ አሥተዳደር ለዳሞት ከነማ እግር ኳስ ክለብ አሠልጣኝ ዘነበ አሰፋ ላበረከቱት አስተዋጽኦ ዕውቅና በመስጠት የፍኖተ ሰላም ከተማ ስታዲየም በር በስማቸው እንዲጠራ አድርጓል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here